ቀጥታ፡

ምርት ገበያ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላችው የግብርና ምርቶችን አገበያየ

መቱ ሚያዝያ  1/2011 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላችው የተለያዩ የግብርና ምርቶች ማገበያየቱን አስታውቀ።

የምርት ገበያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ እንደገለጹት ግብይቱ የተፈጸመው በሀገሪቱ የተለያዩ  አካባቢዎች በሚገኙ 22 ማዕከላት ነው።

በእነዚህ ማዕከላት አማካኝነት የተገበያዩት  ከ502ሺ 600 ቶን በላይ የሚሆኑ ቡና፣ሰሊጥ ፣ አኩሪ አተር፣በቆሎ፣አደንጓሬ፣ ቦሎቄ፣ሽምብራ አና  የስንዴ ምርቶችን እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ግብይት ከተፈጸመባችው   ምርቶች ከ218ሺ284 ቶን በላይ በማገበያየት   ቡና ቀዳሚው ሲሆኑ  ሰሊጥና ነጭ ቦሎቄ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ይከተላሉ።

ግብይቱ የተፈጸመው 20ሺ በሚሆኑ ደንበኞቹና አገናኝ አባላት መካከል እንደሆነ ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

በግብይቱም ከሶሰት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አርሶአደሮች ተጠቃሚ እንደሆኑ አስረድተዋል።

የምርት ገበያው ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳሉት ከ2009 ዓ.ም. የወጣውን የግብይት ስርዓት ማሻሻያ ተከትሎ የምርት መገኛ ቦታ እና የምርት ባለቤት ገላጭ አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል።

በዚህም ምርት ወደ ግብይት ማዕከሉ ሲገባ ማን እንዳስገባውና የት ቦታ እንደተመረተ የሚያሳይ መረጃ መካተቱን ገልጸዋል።

ምርት ገበያው ግብይቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ አርሶአደሩ ሶስተኛ ወገን ሆኖ ምርቱን  ቀጥታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ  የሚያስችለውን አዲስ አሰራር ለመጀመር  ዝግጅት እያደረገ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር  አብይ አህመድና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ለማ መገርሳ በተገኙበት ሰሞኑን ምርት ገበያው  በመቱ ከተማ ለሚያስገነባው 23ኛ ቅርንጫፍ የግብይት ማዕከል የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወሳል፡፡

በዚህ ወቅት እንደተገለጸው ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ  በ3ሺ200 ካሬሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው የግብይት ማዕከሉ  የአካባቢውን የቡና ምርታማነት ጥራት  በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት አስር  ዓመታት ውስጥ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ከአምስት ሚሊዮን ቶን በላይ የተለያዩ ምርቶች ማገበያየቱም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም