በአፍሪካ ቮሊቦል ውድድር ወላይታ ድቻ አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ቮሊቦል ውድድር ወላይታ ድቻ አሸነፈ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2011 በአፍሪካ የቮሊቦል የክለቦች ውድድር የኢትዮጵያ ደርቢ ወላይታ ድቻ ሙገር ሲሚንቶን አሸነፈ።
በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን አስተናጋጅነት በግብጽ ካይሮ ከመጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለው 38ኛው የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን ይዟል።
በውድድሩ 22 ክለቦች እየተካፈሉ የሚገኙ ሲሆን ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ ኢትዮጵያን ወክለው በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ሁለቱ የኢትዮጵያ የቮሊቦል ክለቦች ትናንት ከ17ኛ እስከ 20ኛ ያለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ በአል ሃሊ የቮሊቦል ጂምናዚየም ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻ ሙገር ሲሚንቶን በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 2 አሸነፈ።
2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ የፈጀው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በጂምናዚየሙ የተገኙትን ተመልካቾች ያዝናና እና እስከ መጨረሻው ውጤት ድረስ እልህ አስጨራሽ ፉክክር የተደረገበት መሆኑን የአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን በድረ ገጹ አስፍሯል።
በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሙገር ሲሚንቶ 25 ለ 23 ያሸነፈ ሲሆን በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻ 25 ለ 21 አሸነፈ።
በሶስተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሙገር 25 ለ 19 አሸንፎ 2 ለ 1 መምራት ቢችልም በአራተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻ 25 ለ 14 በሆነ ውጤት በማሸነፍ አቻ መሆን ችሏል።
አሸናፊውን ክለብ ለመለየት የአምስተኛ ዙር ጨዋታ ያስፈለገ ሲሆን ወላይታ ድቻ በሁለት ነጥብ ልዩነት 22 ለ 20 በማሸነፍ የአፍሪካ የቮሊቦል የክለቦች ውድድር ከፍተኛ ፍልሚያና የማሸነፍ ስሜት የታየበትን የኢትዮጵያ ደርቢ ማሸነፍ ችሏል።
ሁለቱ ክለቦች ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በዘንድሮው የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻ 3 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።
በዚሁ ጨዋታ ላይ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻ ሙገርን 42 ለ 40 ያሸነፈበት ነጥብ በኢትዮጵያ የቮሊቦል ታሪክ በአንድ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከፍተኛ ነጥብ የተመዘገበበት እንደነበርም ይታወሳል።
ጨዋታው ከ2 ሰዓት በላይ የፈጀና ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር የተገኘበትም ነበር።
ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ በቮሊቦል ፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ያሳዩትን ጠንካራ ፉክክርና አዝናኝ ጨዋታ ትናንትም በአል ሃሊ ጂምናዚየም ደግመውታል።
ውጤቱንም ተከትሎ ወላይታ ድቻ በውድድሩ ሶስተኛ ድሉን ያስመዘገበ ሲሆን ከዚህ በፊት የዴሞክራቲክ ኮንጎውን አርዲ ኤስፖይርንና የቡሩንዲውን ሩኪንዞን ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በአንጻሩ ሙገር ሲሚንቶ በውድድሩ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደ ሲሆን ከዚህ በፊት በግብጹ አል ሃሊ፣ በሊቢያው አል ሃሊ ትሪፖሊ፣ በቦትስዋናው ፖሊስ ቪአይና በኮትዲቭዋሩ ኤኤስ ኢንጄስ ተሸንፏል።
ሙገር ሲሚንቶ ከትናንት በስቲያ ከ17ኛ እስከ 24ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ባደረገው ጨዋታ የጊኒውን ኤኤስ ፋግን 3 ለ 0 በማሸነፍ በውድድሩ ታሪክ የመጀመሪያ ድሉን ማስመዝገብ መቻሉም ይታወሳል።
ሁለቱ ክለቦች በአፍሪካ የቮሊቦል የክለቦች ውድድር ዛሬ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በዚሁ መሰረት ወላይታ ድቻ በአል ሃሊ ጂምናዚየም 17ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ከማዳጋስካሩ ጌንዳርማሪ ጋር የሚጫወት ሲሆን ሙገር ሲሚንቶ 19ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ከዴሞክራቲክ ኮንጎው ቪኤስ ምዋንጋዛ ጋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጫወታል።
ትናንት በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር በተደረጉ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች የግብጹ አል ሃሊ የሊቢያው አል ስዌህሊን ሌላኛው የግብጽ ክለብ ስሞሃ የሊቢያን አል ሃሊ ትሪፖሊን በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፈዋል።
የግብጹ አል ሃሊ በውድድሩ ታሪክ ለ14ኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት ስሞሃ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ ለመሆን ነገ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በአል ሃሊ የቮሊቦል ጂምናዚየም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይፋለማሉ።
የሊቢያዎቹ ክለቦች አል ስዌህሊና አል ሃሊ ትሪፖሊ ለደረጃ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ በአል ዓሊ የቮሊቦል ጂምናዚየም የሚጫወቱ ይሆናል።
ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ በአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር እያደረጉት ያለው ተሳትፎ በመድረኩ የኢትዮጵያ ስም በቮሊቦል እንዲጠራ ያደረገና ወደፊት ስፖርቱን ሊያሳድጉ የሚችሉ ስራዎች ከተሰሩ የኢትዮጵያ ክለቦች በአፍሪካ መድረክ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ያመላከተ ነው።
የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ነግሰው የታዩበት 38ኛው የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ነገ ፍጻሜውን ያገኛል።
ባለፈው ዓመት በግብጽ ካይሮ በተካሄደው 37ኛው የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር የአገሪቷ ክለብ አል ሃሊ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።
የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር እ.አ.አ በ1987 የተጀመረ ሲሆን የግብጹ አል ሃሊ 13 ጊዜ፣ የቱኒዚያው ሲኤስ ሰፋክሲያን 6 ጊዜ እንዲሁም የግብጹ ዛማሌክ 5 ጊዜ አሸናፊ ሆነውበታል።