ለተፈናቃዮች ድጋፍ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ የቶምቦላ ሎተሪ ሽያጭ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለተፈናቃዮች ድጋፍ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ የቶምቦላ ሎተሪ ሽያጭ እየተካሄደ ነው
ነቀምቴ ግንቦት 25/2010 በሱማሌ እና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ በምስራቅ ወለጋ ዞን የቶምቦላ ሎተሪ ሽያጭ እየተካሄደ ነው፡፡ የዞኑ ምክትል አስተዳደሪ አቶ ገመቺስ ተመስገን እንደገለጹት ተፈናቀይ ወገኖኝን ለማቋቋም የአካባቢው ሕዝበ ላለፉት ስምንት ወራት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህንን ድጋፍ ለማጠናከርም በሎተሪው ሽያጭ ባለሃብቶችና ሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 20 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል። የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት የአካባቢው ነዋሪ አቶ ተካለኝ ቡሊ በሰጡት አስተያየት የተቸገሩ ወገኖችን መርዳትና የተራቆቱትን ማልበስ የኦሮሞ ባህል በመሆኑ እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። አቶ ተካለኝ እንዳሉት ከአንድ ወር ደመወዛቸው ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የዚሁነዋሪ አቶ ግርማ ምትኩ በበኩላቸው ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሎቶሪ በመግዛት ድጋፍ መድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በቶምቦላ ሎተሪ ሽያጭ መክፈቻ ስነ ስርዓት ወቅት የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት የ20 ሺህ ብር፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰራተኞችም ደግሞ የ5 ሺህ ብር ሎተሪ ገዝተዋል። የዞኑ ውሃ፣ ማዕድን፤ ኢነርጂ እና የኢኮኖሚ ልማት ትብብር መስሪያ ቤቶችም የ15 ሺህ ብር ቶምቦላ ለመግዛት ወሰነዋል። የቶምቦላ ሎተሪ ሽያጩ ለሶስት ወራት ይቆያል ተብሏል። የምስራቅ ወለጋ ህዝብ ለተፈናቃይ ወገኖች ለማቋቋም ድጋፍ የሚውል እስካሁን ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉም ተመልክቷል።