በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከ5ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የህክምና አገልግሎት ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከ5ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የህክምና አገልግሎት ተሰጠ
ጎንደር ግንቦት 25/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በእንፍራንዝ ጤና ጣቢያ ከፍለው የመታከም አቅም ለሌላቸው ከ5ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የህክምና አገልግሎት በዘመቻ ተሰጠ፡፡ ተቀማጭነቱ በአሜሪካን ያደረገው ጂዊሽ ቮይስ የተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር አዳነ በራሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት ድርጅታቸው ህብረተሰቡ በጤና ጣቢያ ደረጃ ማግኘት ያልቻለውን ህክምና በቅርብ እንዲያገኝ ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡ "ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ 5ሺ ሰዎች ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል " ያሉት ዶክተር አዳነ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው በዚሁ ዘመቻ 10ሺህ ሰዎች ህክምናውን እንደሚያገኙ አስታውቀዋል፡፡ ኢትጵያዊያንና የውጪ ዜጋ በሆኑ 60 የህክምና ስፔሻሊስቶች አማካኝነት የጥርስ፣ የዓይን ቆብ ቀዶ ህክምና፣ የማህጸንና ጽንስ፣ የውስጥ ደዌ፣ የወንዶች ግርዛትና መለስተኛ ቀዶ ህክምና አገልግሎት በነጻ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የህክምና ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ሶስት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች በመዘዋዋር ነጻ የህክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በእንፍራንዝ ጤና ጣቢያ የተሰጠው ነጻ የህክምና ድጋፍ በአማካይ የአንድ ታካሚ የህክምና ወጪ 35 ዶላር እንደሚደርስ ዶክተር አዳነ ገልጸዋል፡፡ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከነጻ የህክምና ድጋፍ በተጓዳኝ ለእንፍራንዝ ጤና ጣቢያ ግምቱ 100ሺህ ብር የሆነ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የጤና ጣቢያው ኃላፊ አቶ አለሙ ጥሩነህ በበኩላቸው በአካባቢው የውስጥ ደዌ፣ የጥርስና የዓይን በሽታዎች በስፋት እንደሚከሰቱ ጠቁመው "የህክምና ድጋፉ የጤና ጣቢውን ጫና ለመቀነስ የሚያስችል ነው" ብለዋል፡፡ በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ አንዱን የዓይን ብርሃናቸውን አጥተው የቆዩት አርሶአደር ሞገስ አበራ "ባገኙት ነጻ የዓይን ህክምና ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ አርሶአደር ላቂያው ሙጨ በሰጡት አስተያየትም በጥርስ ህመም ሲሰቃዩ ቆይተው በጤና ጣቢያው በተደረገላቸው የህክምና እርዳታ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡