'ክብር ጊዜ ክብር ሰው' የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በቃ

አዲስ አበባ መጋቢት30/2011 በደራሲ ሙሉ ሰለሞን የተዘጋጀው 'ክብር ጊዜ ክብር ሰው' የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በቃ።

'ክብር ጊዜ ክብር ሰዉ' የተሰኘው መፅሃፉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስተር፤ የገቢዎች ሚኒስተር ዴኤታ፤ አምባሳደሮች ፤ የጥበብ ሰዎች ፤ጋዜጠኞች እና የኃይማኖት አባቶች በተገኙበት ትናንት ማምሻውን ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።

በጀርመን ሀገር የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን በቅርቡ የተሾሙት  ደራሲ ሙሉ ሰለሞን ጊዜ ማለት በቀን ፣በሰዓት በሴኮንድ የተቀመጠ ብቻ ሳይሆን  የሰው ልጅ ህይወት ነው፤ ጊዜን ማክብር እራስንና ሰውን ማክበር ነዉ፤ ሴኮንድንም ቢሆን ማባከን የለብንም ብለዋል።

ደራሲ አምባሳደር ሙሉ አክለውም በጀርመን ሀገር የሚገኙ ታሪካዊ መፅሀፎችን የማስመልስ፤ የሀገራችን እሴቶች እና ባህሎችን በማስተዋወቅ የባህል ኢንዱስትሪውን ማሳደግ የሀገሪቱን የዉጭ ምንዛሪ ማጎልበትና ኢኮኖሚውን የማሳደግ ስራም እንደሚሰሩም  ተናግረዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳዉ  በጀርመን  ሀገር ያሉ በርካታ ታሪካዊ መፅሃፍት ወደ ሀገራችን እንዲመለሱና አሁን ያሉትን የተፈጥሮ እና ሰዉ ሰራሽ ቅርሶችን በማስተዋወቅ የገቢ ምንጭን የማሳድግ ስራ እንዲሰራ አሳስበዋል።

ዶክተር ሂሩት አክለውም "በጀርመን ሀገር የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸዉ ታሪካዊ መፃሕፍት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ መሰራት አለበት" ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶችም የተዘጋጀውን መፅሃፍ  ተከታዮቻቸዉን እንደሚያስተምሩበት በመናገር ሰዓት ማክበር በዓለማዊ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ህይወትም ትልቅ ዋጋ እንደሚያሰጥ አብራርተዋል።

የባህል እና የፍልስፍና መነሻችን ሃይማኖት  በመሆኑም በኃይማኖት ቦታዎች ሰዓት ማክበር ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠዉ ጉዳይ እንደሆነም ተጠቁሟል።

አምባሳደርና ደራሲ  ሙሉ ሰለሞን ጊዜና ሌሎች ጥቅሞች በአማረኛና በከፊል እንግሊዘኛ፣ እጣ  የአጫጭር ልብ ወለዶች (በጋራ የታተመ) ፣ ስንክ ፍሬ ቅኔዎች፣ ሲንቢሮ የኦሮሞኛ ግጥሞችና ቅኔዎች እና አሁን ለምረቃ የበቃውን 'ክብር ጊዜ ክብር ሰው' መፅሃፎችን ለንባብ አብቅተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም