የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደብረብርሃን ከተማ ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደብረብርሃን ከተማ ወጣቶች ገለጹ
ደብረብርሀን መጋቢት 30/2011 የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስከበር ከመንግስት ጎን ተሰልፈው የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደብረብርሃን ከተማ ወጣቶች ገለጹ፡፡
ወጣቶቹ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ የተቀሰቀሰውን ግጭት በመቃወም ዛሬ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
የሰልፉ አስተባባሪ ወጣት እዮብ ፋንቱ በአካባቢያቸው የሚደርሰውን የኃይል ጥቃት ተደራጅተው ለመመከት እንደሚሰሩ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ከከተማው የተወጣጡ ወጣቶች በየደረጃው ካሉ የመንግስት አካላት ጋር በመተባበር የአካባቢቸውን ሰላምን ለማስከበር የሚያግዝ አስር አባላት ያሉት ኮሚቴ ማቋቋማቸውን አመልክቷል፡፡
የተቋቋመው ኮሚቴ በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ ጭምር እንደሆነ የጠቀሰው አስተባባሪው ችግሩን ለመፍታት ከመንግስት ጋር እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
የከተማው ነዋሪ አቶ ማሙሸት አማራ በበኩላቸው በተፈጠረው ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም በሰላማዊ ሰልፍ ሰበብ ሁከት ለመፍጠር መንቀሳቀስ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸው ወጣቱ እርስ በእርስ በመተጋገዝ ችግሩ እንዳይባባስ ማድረጉ እንደሚደገፍ አስረድተዋል፡፡
አቶ ማሙሸት " ከመንግስት ጎን በመቆም የአካባቢን ሰላም ለማስጠበቅ በጋራ እንሰራለን " ብለዋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድም አገኝ በኤፍራታና ግድም እና አፆኪያና ገምዛ ወረዳዎች በተከሰተው ግጭትና በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአካባቢው ልዩ ኃይል ፣ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት በጥምረት ባደረጉት ሰላም የማስከበር ስራ አሁን አካባቢው መረጋጋቱን አስታውቀዋል፡፡
በደበረብርሃን ከተማም መንግስት የዜጎችን ህይወት ይጠብቅ በሚል በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ሌላ አጀንዳ ያላቸው ወገኖች የወጣቱን ቅን ልቦና ለመበረዝ የተደረገው እንቅስቃሴ አሳፋሪ እንደሆነ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡
በጥቂት ግለሰቦች ሀሳብ የከተማዋን ሰላም ማደፍረስና የነዋሪዎችን ፀጥታ መንሳት ተገቢ አለመሆኑን በመገንዘብ ህዝቡ የአካባቢውን ፀጥታ ነቅቶ በመጠበቅ መንግስትን እንዲደግፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በቀጣይ ነዋሪዎችን በማሳተፍ ውይይት እንደሚደረግም አመልክተዋል፡፡
በዞኑ ኤፍራታና ግድም ወረዳ የተከሰተው ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡