በገብረጉራቻ ከተማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በገብረጉራቻ ከተማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ
ፍቼ ግንቦት 25/2010 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረጉራቻ ከተማ ዛሬ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ አደጋው የደረሰው ዛሬ ከረፋዱ አራት ሰዓት ተኩል አካባቢ በከተማው በተለምዶ ምሳሌ ራስ ተብሎ በሚጠራው ሠፈር የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 92588 ኢት ሀገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ 65 ሰዎችን አሳፍሮ ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር ከተማ በማምራት ላይ እንዳለ በአንድ ባጃጅ ተሽከርካሪ ላይ በመውጣቱ ነው፡፡ የዞኑ ፖሊስ የትራፊክ ደህንነትና ቁጥጥር የስራ ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጅን ታደለ ሌጅሶ ለኢዜአ እንደገለጹት በአደጋው ህይወታቸው ያለፈው የባጃጅ አሽከርካሪና ያሳፈራቸው ሁለት ሰዎች ናቸው፡፡ በባጃጁ ተሳፍረው የነበሩ ሌሎች ሁለት ሰዎችም ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በገብረጉራቻ ጤና ጣቢያ የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸው መሄዳቸውን አመልክተዋል፡፡ የአደጋው መንስኤ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በከተማው ውስጥ ከልክ በላይ ሲያሸከረክር መሆኑን ዋና ሳጅን ታደለ ጠቁመው በአውቶብሱ ተሰፍረው የነበሩ ሰዎች በሌላ ተሸከርካሪ ተሸኝተው አሸከርካሪው በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆይ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡ በከተማው ተማሪዎች በሚለቀቁበትና በገበያ ቀናት አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን በልክ ቢያደርጉ እራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ከጉዳት ማዳን እንደሚችሉ መክረዋል።። ፖሊስ በአደጋው የሞቱትን ሰዎች አስከሬን ለምርመራ ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል መላኩን ተመልክቷል።