ቤተክርስታኗ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ 31 ሚሊዬን ብር በላይ ድጋፍ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ቤተክርስታኗ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ 31 ሚሊዬን ብር በላይ ድጋፍ አደረገች
አዲስ አበባ መጋቢት 30/2011 ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ 31 ሚሊዬን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን አስታወቀ።
ባለፈው አንድ ዓመት ባደረገው ድጋፍም ከ52 ሺህ በላይ ለተፈናቃይ ዜጎችን መድረስ መቻሉን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን 15ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።
በጉባኤውም ኮምሽነሩ አቶ ግርማ ቦሪሼ የኮሚሽኑን የአንድ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
ኮሚሽኑ ድጋፍ የሚሹና ከድህነት ወለል በታች ያሉ ዜጎችን የሚረዳና ጾታን መሰረት አድርጎ ጥቃት ለደረሰባቸውን ዜጎች ከለላ የሚሰጥ ነው።
በጎጂና ልማዳዊ ድርጊቶችም አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች አንዲያገግሙ የሚያግዝና መሰረተ ልማተ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ግንባታ የማከናወንና ድጋፍ የመስጠት ስራን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ግብረ ሰናይ ኮሚሽን መሆኑንም ተናግረዋል።
ከተቋቋመበት ዓላማ ጎን ለጎንም ባለፈው አንድ ዓመት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭተ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ 52 ሺህ 602 ዜጎችን የመደገፍና መልሶ የማቋቋም ስራዎችን በ31 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር አከናውኗል።
በጌዴኦና ምእራብ ጉጂ ዞኖች በቀርሜ፣ በገደብ፣ በኮቸሬና በይርጋለም አካባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች 11 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በኦሮሚያና ሱማሌ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ ዜጎችም 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ምግብና የቤት እንስሳትን በመግዛት ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው 16 ሚሊዮን ብር የፈጀ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በማድረግም ከ10 ሺህ በላይ ዜጎችን በዘላቂነት ማቋቋም መቻሉን ነው የተናገሩት።
ሌላው በምሰራቅና ምእራብ ወለጋ ዞኖችም እንዲሁ ከሳቢጋ፣ ነጆ፣ ቂልጡ ካራና መነሲቡ አካባቢዎች ላይ ለሰፈሩ 3ሺህ ተፈናቃይ ዜጎች በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን እንዲሁ።
በተያያዘም ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎችን ለማቋቋም የሚያስችሉ 238 ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በስራ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቶቹ ሙያዊ ስልጠናዎችን በመስጠትና መነሻ ካፒታላቸውን በመደጎም ወደ ስራ አንዲገቡ የሚያስችል፣ የአካባቢ ደህንነትና የልማት ስራዎች ላይ በሰፋት የሚያሳትፉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ለዚህም ደግሞ 170 ሚሊዮን ብር ተበጅቶ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎችም እንዲሁ በተለያዩ አካባቢዎች 46 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 128 ምንጮችን በማጎልበትና በእጅ የሚሰሩ ፓምፖችን በመገንባት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በትምህርት ዘርፍም 27 ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ክልሎች ተቋቁሟል ያሉት ኮሚሽነሩ ከዚህ ውስጥ ሰባት ትምህርት ቤቶች የልዩ ትምህርት ፍላጎት ላላቸው ታስበው የተገነቡ ናቸው ይላሉ።
በዚህም ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው 13 ሺዎቹ የልዩ ትምህርት ፍላጎት ተጠቃሚ ሆነዋል።
በተጨማሪም በጤናና ስነ-ምግብ ፕሮግራም 27 ፕሮጀክቶች የተካሄዱ ሲሆን ሶስት የጤና ተቋማትን ማቋቋም መቻሉንም አክለዋል።
24ቱ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልገሎት ላይ ያተኮሩና የእናቶችና የህጻናት ሞትን ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በዚህም ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የቤተክርስቲያኗ ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ከአካባቢው ምሁራን፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ጋር ሰላምን በዘላቂነት በማስፈን ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ወጣቱ ትውልድ ትኩረቱን ልማት ላይ እንዲያደርግም የማገዝና አመለካከቱን እንዲቀይር የሚያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጫና የስልጠና ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል ቤተክርስቲያኗ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንደምትሰራ አመላክተዋል።