በጋምቤላ ክልል እያገጠመ ያለው የበጀት እጥረት የገቢ አሰባሰብና እቅድ ላይ ባሉ ክፍተቶች መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል እያገጠመ ያለው የበጀት እጥረት የገቢ አሰባሰብና እቅድ ላይ ባሉ ክፍተቶች መሆኑ ተጠቆመ
ጋምቤላ መጋቢት 30/2011 በጋምቤላ ክልል በየዓመቱ እያጋጠመ ያለው የበጀት እጥረት የተለጠጠ የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ ለብክነት የተጋለጠ የገቢ አሰባሰብና እቅድን መሰረት ያላደረገ አጠቀቀም ክፍተቶች መሆኑ ተጠቆመ።
የጋምቤላ የኒቨርሲቲ ለክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በበጀት አጠቃቀምና በአመራርነት ዙሪያ ጥናትን መሰረት ያደረገ የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡጁሉ አኮክ በስልጠናው ላይ ባቀረቡት ጥናታዊ ጹሁፍ እንዳመለከቱት በክልሉ እያጋጠመ ላለው የበጀት እጥረት መንስኤው በመንግስት መስሪያ ቤቶች ያለው የተለጠጠ የሰው ኃይል አደረጃጀት አንዱ ነው፡፡
ለብክነት የተጋለጠ የገቢ አሰባሰብ ፣ እቅድን መሰረት ያላደረገ የበጀት አጠቀቀም እና በየጊዜው የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ዶክተር ኡጁሉ በጥናታዊ ጹሁፋቸው የጠቆሟቸው ሌሎች ክፍተቶች ናቸው፡፡
በነዚህም ምክንያቶች በክልሉ የሚሰበሰበው ውስን ገቢና በፌዴራል መንግስት የሚመደበው የድጎማ በጀት ከሰራተኛ ደመወዝና ከስራ ማስኪያጃ የሚያልፍ ባለመሆኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንደማይቻል ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት አቅምን ያገናዘበ የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ ጠንካራ የገቢ አሰባሰብ ስርዓትና እቅድን መሰረት ያደረገ የበጀት አጠቃቀም መተግበር ካልቻለ የበጀት እጥረቱ ሊቃለል እንደማይችል በጥናታዊ ጹሁፋቸው አመላክተዋል ።
ከተሳታፊ አመራሮች መካከል አቶ ኡቻላ ቻም በሰጡት አስተያየት "የክልሉ የገቢ አሰባሰቡ ለብክነት የተጋለጠና የግለሰቦች መጠቀሚያ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የገቢ ሰብሳቢ ሙያተኞች በዘርፉ የሰለጠኑ አይደሉም " ብለዋል።
በዚህም ምክንያት የክልሉ የገቢ አቅም ሊያድግ አለመቻሉን ጠቁመው የገቢዎች ባለስልጣን ቢሮ የሰው ኃይል አደረጃጀቱን ማሻሻል እንዳለበት ጠቁመዋል ።
"የቀረበውን ጥናታዊ ጹሁፍ መንግስት በፖሊሲው አካቶ መስራት ከቻለ በክልሉ ለበጀት እጥረት በመንስኤነት የተጠቀሱት ችግሮች ሊቃለሉ ይችላሉ " ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ አኳይ አቡቲ ናቸው።
በክልሉ በተለይም የሲቪል ሰርቪሱ አወቃቀር ያልተማከለ በመሆኑ በዞንና በወረዳዎች አግባብነት የሌለው ከፍተኛ የሰራተኛ ቅጥርና ምደባ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል ።
የክልሉን የበጀት እጥረት ለመፍታት በጥናታዊ ጹሁፉ የተጠቆሙ ምክር ሃሳቦችን በፖሊሲ አካቶ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መሰተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ጥናታዊ ጹሁፉ የክልሉን የበጀት እጥረት መንስኤዎች በትክክል የለየና ያመለከተ ነው።
ጥናቱን በፖሊሲ በማካተት የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በጥናቱ ለበጀት እጥረቱ ከተጠቀሱት ችግሮች የተለጠጠ የሰው ኃይል የተባለው ትክክል መሆኑን አመልክተው ይህ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድን ያላገናዘበ ከፍተኛ የስራ መደብ መካሄዱ ሌላው ተጨማሪ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።
በጋምቤላ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ትናንት ተጠናቋል።