ቀጥታ፡

የመምህራን አገልግሎት ኮሚሽን ሊቋቋም ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2011 በመምህራን ጉዳዮች ላይ የሚሰራ የመምህራን አገልግሎት ኮሚሽን ሊቋቋም መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

"ገበሬ ዘር ሲዘራ መጀመሪያ መሬት ያለሰልሳል። ከዚያም ይዘራል" የሚሉት የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ደበበ ገብረጻድቅ፤ ከትምህርት ፍኖተ ካርታውና ስርዓተ ትምህርቱ ዝግጅት  በፊት ዘር እንደሚያበቅል መሬት የምንቆጥረው አስተማሪውን ነው ይላሉ።

አዕምሯዊና ማህበራዊ ደህንነት የሚሰማቸው መምህራን ሳይኖሩ በስርዓተ ትምህርት ብቻ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልጸው፤ የመምህራን የፍትህ ጥያቄዎች በዘላቂነት ሊመለሱ እንደሚገባም ይናገራሉ።

ከ36 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች እያስተማሩ ለሚገኙ ከ5 መቶ ሺህ በላይ መምህራን "አገሪቷ ተመጣጣኝ ክፍያ የላትም" የሚለው አስተያየት በማህበሩ በኩል ተቀባይነት ስለሌለው መንግስት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አንዳለበትም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ በንቲ በበኩላቸው ማኅበሩ የአባላቱን መብትና ጥቅሞች እንዲከበሩ ጥረት ማድረጉን ተናግረው፣ በደረጃ መሰላልና በመኖሪያ ቤት ጥቅማ ጥቅሞች ጅምር ስራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

"የመምህራን መኖሪያ ቤት ጉዳይ የመስርያ ቦታም ጭምር ነው" ያሉት ዶክተር ዮሃንስ፤ በተለይም በአዲስ አበባ ያሉ መምህራን ከባድ የቤት  ችግር ያላቸው በመሆኑ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እንዲሟላ ከከተማ አስተዳድሩ ጋር ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።

የአስተማሪነት ሙያ ብዙ ከማውራትና ብዙ ከመቆም ጋር ተያይዞ ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንደሚያጋልጥም የገለጹት አቶ ደበበ፤ የጤና ዋስትና ባለመኖሩም በርካታ መምህራን የጡረታ ዕድሜያቸው ሳይደርስ በበሽታ ምክንያት እንደሚሰቃዩ ተናግረዋል።

ከ100 በላይ የሚሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅት ሰራተኞች የጤና ዋስትና እንዳላቸው በማስታወስ፣  ትውልድ ለሚቀርጹ ሙያተኞችም የጤና ዋስትናም ሊኖራቸው እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ዶክተር ዮሐንስ በበኩላቸው የትምህርትን ጥራት ለማሻሻል የትምህርት ሙያተኛውን ኑሮ ማሻሻል እንደሚገባ ገልጸው፤ ዘርፉን ለመምራት ከሲቪል ሰርቪስ የተለየና ተጠሪነቱም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ ኮሚሽን እንዲቋቋም ጠይቀናል ብለዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ ካለ መምህራን ተሳትፎ ስርዓተ ትምህርቱን መተግበር እንደማይቻል ያምናሉ።

ፍኖተ ካርታው አጠቃላይ የትምህርትና ስልጠና ሰርዓቱን እንደሚፈትሽ ገልጸው፤ ከነዚህም መካከል የመምህራንን ጉዳይ ከምልመላ እስከ ጡረታ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ የመምህራን አገልግሎት ኮሚሽን ሊቋቋም መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኮሚሽኑ በጥናት ላይ ተመስርቶ የመምህራንን ጥቅማ ጥቅም ለማሰከበር በዝርዝር እንደሚሰራ ገልጸው፤ አሁን ላይ ኮሚሽኑን ለማቋቋም ምክረ ሃሳብ ቀርቦ የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሚመለከታቸው አካላት ሃሳብ ተሰጥቶበት የትምህርት ማኅበረሰቡን አደረጃጀት፣ ዲሲፒሊኑን እንዲሁም፣ ጥቅማ ጥቅሙን በሚመለከት ነጻ በሆነ አካል ተጠንቶ የሚቋቋመው ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለፓርላማ እንደሚሆንም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም