አምባሳደር ሱሌይማን የሹመት ደብዳቤያቸውን ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አቀረቡ

125

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2011 በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ የሁለቱ አገራት ጠንካራ ወዳጅነት ወደ ላቀ ከፍታ እንዲሸጋገር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ አስታወቁ፡፡

አምባሳደሩ ትናንት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለአገሪቷ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሳሪ ማዞሪ አቅርበዋል።

በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ቆይታቸውም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር ተግተው እንደሚሰሩ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡

አምባሳደር ሱሌይማን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋርም የትውውቅ ፕሮግራም አካሂደዋል።

ዜጎችን ለስደት እየዳረገ ያለውን ድህነትና የመልካም አስተዳደር ጉድለት በጋራ መታገል እንደሚገባ በዚሁ ጊዜ በአጽንኦት ተናግረዋል አምባሳደሩ፡፡

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አህመድ ሳሪ በበኩላቸው የአገራቱ ግንኙነት ጠቃሚና ታሪካዊ መሆኑን ገልጸው ለንግድና ኢንቨስትመንት ትኩረት በመስጠት ለጋራ ተጠቃሚነት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ የተገኙ ተሳታፊዎችም አገራቸውን በሚችሉት ሁሉ ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለፃቸውን የጽሕፈት ቤቱ መግለጫ ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም