በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ህይወታቸውን ላጡ ስርዓተ ፀሎት ተከናወነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ህይወታቸውን ላጡ ስርዓተ ፀሎት ተከናወነ
አዲስ አበባ መጋቢት 29/2011 በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ዛሬ በአዲሰ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ስርዓተ-ፀሎት ተከናወነ።
ስርዓተ ፀሎቱን በራስ ተነሳሽነት ያዘጋጁት ጉዳዩ ይመለከተናል ያሉ የተለያዩ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ልክ የዛሬ ወር ገደማ ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ቢሾፍቱ አካባቢ ተከስክሶ 17 ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ለ157 ሰዎች ህልፈት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።
በአደጋው ያዘኑና ሀዘናቸውንም መግለፅ የፈለጉ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ባስተባበሩት በዚህ ጸሎት ስነ-ስርዓት ላይ የተጎጂ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም የአየር መንገዱ ሰራተኞች ተገኝተዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይም ህይወታቸውን ላጡት ጸሎትና የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት እንዲሁም ጸበል ጻድቅ ተዘጋጅቷል።
አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው እንዳልተለያቸው የገለፁት የሟች ቤተሰቦች ለተደረገላቸው ሁሉ በዚሁ ወቅት አመስግነዋል።
ከአደጋው ሰለባዎች መካከል የሆነችው የ24 ዓመቷ የበረራ አስተናጋጅ የወይዘሪት አያንቱ ወላጅ እናት ወይዘሮ ክበቧ ለገሰ '' ኢትዮጵያዊያን አደጋው ካጋጠመበት ጊዜ አንስቶ ከጎናቸው በመሆን እያጽናኑ ያሉበት መንገድ ፍጹም ኢትዮጵያዊነት የተሞላበት ነው'' ይላሉ።
''በዛሬው እለትም ያገባናል ያሉ ኢትዮጵያዊያን ዘር፣ ቀለም፣ ኃይማኖት ሳይለዩ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡትን ልጆቻችንን ማሰባቸውና እኛ ቤተሰቦችን ማጽናናታቸው ብርታት እየሆነን ነው'' ሲሉም ገልፀዋል።
የጸሎት ስነ_ስርዓቱ አስተባባሪ ወይዘሮ ቅድስ አሳልፍ በበኩላቸው፣ በሃዘኑ የተጎዱትን አንዳቸውንም እንደማያውቋቸውና ነገር ግን ''እንደ አንድ ኢትዮጵያዊት እናት ሃዘኑ የሁላችንም ነው'' በማለት መታሰቢያውን ሊያዘጋጁ መነሳታቸውን ገልጸዋል።
አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ስፍራ ነዋሪ ማህበረሰብ አባላት ለሟቾች ሀዘናቸውን የገለፁበትና ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን የተመኙበት ሁኔታ የኢትዮጵያዊያን እውነተኛው መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያዊነት ማለት በሁሉም ነገር መተሳሰርና መተባበር ነው ሲሉ አክለዋል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩልም እየተደረገላቸው ያለውን ድጋፍ ያደነቁት የሟች ቤተሰቦች አደጋው በተከሰተበት ስፍራ ለሟቾቹ የመታሰቢያ ሃውልት ቢቆምላቸው ልባቸው እንደሚያርፍም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የመጀመሪያውን የአውሮፕላኑን የምርመራ ውጤት ይፋ መድረጉን ተከትሎም የቦይንግ ኩባንያ ይቅርታ መጠየቁ እንዳለ ሆኖ ዳግም አሳዛኝ ሃዘን እንዳይከሰትም ኩባንያው ለአገልግሎት የሚያበቃቸውን አውሮፕላኖች ደህንነት በወጉ ሊያጤን እንደሚገባ ቤተሰቦች አሳስበዋል።
አየር መንገዱም በሂደት ላይ ያሉትን የሟቾች ጉዳይ ቸል ሳይል በፍጥነት ተከታትሎ የሚገባውን ሁሉ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።