በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት መቶ ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 2ኛ ዙር የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ሊጀመር ነው

62
አዲስ አበባ  25/2010 አዲስ አበባ ውስጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሁለት መቶ ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛ ዙር የምግብ ዋስትና መርሃ -ግብር ነገ በይፋ እንደሚጀመር ተነገረ። ከዚህ ቀደም  ተግባራዊ የሆነው የመጀመሪያው ዙር መርሃ ግብር በአስር ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ 124 ሺህ የደሃ ደሃ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን ከተጠቃሚዎቹ መካከልም 63 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው። በሚሊኒየም አዳራሽ ነገ በይፋ የሚጀመረው ሁለተኛው ዙር የምግብ ዋስትና  መርሃ -ግብርም በመዲናዋ ባሉ 55 ወረዳዎች ኑሮአቸውን በዝቅተኛ ደራጃ  የሚገፉ ዜጎችን ያካተተ ነው ተብሏል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚተገበረው ለዚህ የከተሞች ምግብ ዋስትና መርሃ-ግብር  በጠቅላላው 450 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመድቧል። ከዚህ ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላሩ የተገኘው ከአበዳሪ ተቋማት ሲሆን፤ ቀሪው 150 ሚሊዮን ዶላር  በመንግስት የተመደበ ነው። በአጠቃላይ ለመርሃ-ግብሩ ማስፈፀሚያ ከተመደበው ከዚህ በጀት ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚተገበርው መርሃ-ግብር ይውላል። የአዲስ አባባ ከተማ ከንቲባ  ድሪባ ኩማ ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠቃሚዎችን ለመለየት የተቋቋመው ኮሚቴ ከገለልተኛ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥልቅ ማጣራት አድርጓል። "በተደረገው ማጣራትም 200 ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተለይተዋል" ብለዋል። በመዲናዋ 600 ሺህ ዜጎች ኑሯቸው ከድህነት ወለል በታች መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው፤ በአንደኛውና ሁለተኛው ዙር የምግብ ዋስትና መርሃ-ግብር አማካኝነትም ከተጠቀሰው አሃዝ ግማሽ ያህሉ ተጠቃሚ ይሆናል፤ ይህም መንግስት የዜጎቹን ኑሮ ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል። በመርሃ-ግብሩ መሰረት 84 በመቶዎቹ ተጠቃሚዎች በማህበረሰብ አቀፍ ልማት በመሳተፍ ገቢ እንዲያገኙ የሚደረግ ሲሆን ቀሪዎቹ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ናቸው ሲሉም ከንቲባ ድሪባ ገልፀዋል። መርሃ-ግብሩ የተጠቀሱትን የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ  ሁኔታ ከማሻሻል በተጨማሪ በሚከናወኑት የማህበረሰብ አቀፍ የልማት ሥራዎች አማካኝነትም የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳትና ውበት እንዲጎለብት ትልቅ አስተዋጽኦ አንደሚያደርግም ከንቲባው ተናግረዋል። ተጠቃሚዎቹ ከድህነት ወለል ወጥተው በዘላቂነት ኑሯቸውን ማሻሻል እንዲችሉም በመርሃ -ግብሩ አማካኝነት ከሚያገኙት ገቢ እንዲቆጥቡ ይደረጋልም ብለዋል። በመርሃ-ግብሩ ያልተካተቱ ሌሎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችም ወደፊት ተግባራዊ በሚደረጉት የመርሃ-ግብሩ እቅዶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል። በመጀመሪያው ዙር መርሃ ግብር ከታቀፉት የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል 84 በመቶው በማሀበረሰብ አቀፍ ልማት ተሰማርተው ገቢ እያገኙ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ የቀጥተኛ ድጋፍ ተጠቃሚ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም