በአፍሪካ የጎሰኝነት አስተሳሰብን በመዋጋት አንድነትን ለማጎልበት መስራት ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የጎሰኝነት አስተሳሰብን በመዋጋት አንድነትን ለማጎልበት መስራት ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ መጋቢት 29/2011 በአፍሪካ ለዘር ማጥፋት መንስኤ የሚሆኑ የጥላቻና የጎሰኝነት አስተሳሰብን በመዋጋት አንድነትን ለማጎልበት መስራት እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ።
ህብረቱ 25ኛውን የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ መታሰቢያ መርሃ-ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1994 በቱቲሲና ሁቱ የርዋንዳ ጎሳዎች መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በተፈፀመ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ቱትሲ ሩዋንዳዊያን ህይወት ጠፍቷል።
ይህንን ቀን ለማሰብ ተብሎ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ተወካይና የህብረቱ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ቪኮተር ሀስሊ ባስተላለፉት መልዕክት በሩዋንዳ የተከሰተው ዓይነት የዘር ማጥፋት እልቂት ዳግም በአህጉሪቱ እንዳይከሰት የጥላቻና ጎሰኝነት አስተሳሰብን በመዋጋት አንድነትንና አብሮነትን ማጎልበት ይገባል ብለዋል።
ጎሰኝነት፣ አክራሪነት፣ጥላቻን የሚሰብክ ርዕዮተ አለም ማስወገድ በህዝቦች መካከል ያለውን የማህበራዊ ካፒታልና እሴቶችን ለማጎልበት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ሲሉም አክለዋል።
በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ በበኩላቸው ከሩዋንዳ የዘር ማጥፋት አስከፊነት ትምህርት በመውሰድ ዳግም እንዳይከሰት የአሁኑና መጪው ትውልድ ለአገር ግንባታና አንድነት እንዲሰራ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ሩዋንዳ በዘር ማጥፋት ጭፍጨፋው የተፈጠሩ ችግሮችን ማስወገድ በመቻሏ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ስኬት ተጠቃሽ ለመሆን መብቃቱንም አምባሳደሯ ጠቅሰዋል።
"በመሆኑም በሩዋንዳ የተፈጸመውን 25ኛውን የዘር ጭፍጨፋ መታሰቢያ ስናስብ ሩዋንዳዊያን በቀልንና ጥላቻን አስወግደው እንዴት በይቅርታና በመስማማት አብሮነታቸውንና አገራቸውን እንደገነቡ ልምድና ተሞክሮ የምንወስድበት መሆን አለበት" ብለዋል።
በሩዋንዳ ያለውን የአንድነትና የአብሮነት ተግባር ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ማስተማር አንድነት፣ተከባብሮና ተቻችሎ መኖርን ለማሳወቅ እንደሚያግዝ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የሩዋንዳ አምባሳደር ሆፕ ጋሳቱራ ደግሞ አፍሪካዊያን ወጣቶች ባልተገባ የጥፋት መንገድ እንዳይመሩ በሩዋንዳ ከተፈጸመው የዘር ማጥፋት ተግባር አስከፊነት ተገቢውን ግንዛቤ በመጨበጥ መልካም ጎዳናን ይመርጡ ዘንድ ሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ተገቢውን ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት በየዓመቱ ቀኑን ለማክበር መወሰኑ ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰው ይህም አለም አቀፉ ማህበረሰብ በሩዋንዳ ከተፈጠረው አስከፊ ታሪክ ለመማር እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
በተለይም መሰረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶችንና መርሆችን በማስተማር ወጣቶች ለአገር ግንባታ ወሳኝ በጎ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የሃይማኖት አባቶች የሰላም መልዕክት ያሰተላለፉ ሲሆን ለሳምንት የሚቆይ የፎቶ አውደ ርእይም ተከፍቷል።
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1994 በቱቲሲ ጎሳ ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የተካሄደ ሲሆን ሩዋንዳዊያን ገቻቻ በሚባለው የችግር አፈታት ስርዓት ባደረጉት እርቅ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በፈጣን ኢኮኖሚ እድገት ከሚታወቁ አገራት መካከል አንዷ ለመሆን መብቃቷን መረጃዎች ያሳያሉ።