በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል
ጎንደር መጋቢት 29/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ድጋፍ እንዲደረግላቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጠየቀ።
ዩኒቨርሲቲ 29ኛውን የጥናትና ምርምር ጉባዔውን "ጥናትና ምርምር ለፈጠራ ሥራ" በሚል መሪ ቃል አካሄዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሥራዎቹ ችግር ፈቺ እንዲሆኑ እገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡
መንግሥት በዘርፉ የሚታየውን የበጀት እጥረት በመፍታትና የምርምር ማዕከል በማቋቋም በሥራዎቹ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባው ተናግረዋል።
ለሥራዎቹ የሚሰጠው ጊዜ አነስተኛ መሆንም ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት እንዳልተሰጠው ያሳያል ብለዋል።
የምርምር ቁሳቁስ በአገር ውስጥ አለመገኘትና የግዥ ሥርዓቱ አለመሻሻልም እንዲስተካከል ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡
"ዩኒቨርሲቲዎች እውቀት ማስተላለፍን ብቻ ሳይሆን አዲስ እውቀትንም መፍጠር ይገባቸዋል" ያሉት ፕሮፌሰር መርሻ፣ ለምርምር የሚሰጠው ትኩረት በማነሱ አዲስ እውቀት በመፍጠር በኩል ያላቸው ተሞክሮ አናሳ ሆኗል ብለዋል፡፡
የቤተ ሙከራ ህንፃዎች ቁጥር አነስተኛ መሆንና ለተመራማሪዎች የተለየ ማበረታቻ አለመሰጠቱ በዘርፉ ውጤት አለመመዝገቡን ገልጸዋል።
ራሱን የቻለ የምርምር ክህሎት ማዳበሪያ ስልጠና ከመስጠት አንጻር ያለው ክፍተት ሊተኮርበት እንደሚገባም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ኤክሲቲዩቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ በዩኒቨርሲቲዎች ለጥናትና ምርምር ሥራዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባዋል ይላሉ።
ትምህርትና ምርምርን ከአገሪቱ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግና የመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ መስፋፋት እንዳለበትም አመልክተዋል።
ለተመራማሪዎች ማበረታቻና ጊዜ እንዲሰጣቸውም ፕሮፌሰር ጠይቀዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው ሥራዎቹ በሚፈለገው መንገድ ባለመስራታቸውና ችግር ፈቺ ባለመሆናቸው አገሪቱ ከድህነት እንዳትወጣ አድርጓታል ብለዋል።
አውስትራሊያና ካናዳ ከ150 ዓመታት ያልበለጠ ዕድሜ ያላቸው አገሮች ቢሆኑም፤ በጥናትና ምርምር ሥራዎች ታግዘው አዲስ ነገር በመፍጠር መበልጸጋቸውን ለአብነት አስታውሰዋል።
"ያለ ምርምርና አዲስ ነገር መፍጠር እድገት አይኖርም" ያሉት ዶክተር ፈንታ፣ሥራዎቹን ወደ ውጤት መቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጉባዔው እንግዶች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል።