ቀጥታ፡

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር በቴሌቶን ያሰባሰበውን ገንዘብ ተገቢ ለሆኑ የልማት ሥራዎች አውያለሁ አለ

ወልቂጤ መጋቢት 29/2011 የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር በቴሌቶን ያሰባሰበውን ገቢ በአግባቡ ስራ ላይ ማዋሉን ገለጸ።

ማህበሩ በ2002 ዓ.ም ባካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ከ156 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማገኘቱ ይታወሳል።

ይህንን መነሻ ገንዘብ በመጠቀም የጉራጌ ዞን ህዝብና መንግስትን በማስተባበር 38 ፕሮጀክቶችን ነድፎ ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸውን አጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲውሉ አድርጓል።

የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አለሙ ዘበርጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቶቹን በማስፈጸም፣ በቅርበት በመከታተልና ለአገልግሎት እንዲበቁ በማስቻል ረገድ ህዝቡና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር።

በቴሌቶን የተሰበሰበውን ገቢ እንደ መነሻ በመጠቀም ከህዝቡና ከተለያዩ ተቋማት በተገኘ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ በጉራጌ ዞን ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች 640 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት ባለፉት ዓመታት የመጠጥ ውሃ፣ የመንገድ ጥገናና ግንባታ፣ የወጣት ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶችን የማሳደግና የማስፋፋት፣  የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ግንባታ፣ የህዝብ ቤተ-መጽሐፍት፣ የችግኝ ጣቢያ ማቋቋም ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል።

በተጨማሪም በወልቂጤ ከተማ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ለማስወገድ ተግባር የሚውሉ ሁለት ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች መገዛታቸውም ተመልክቷል።

ተሽከርካሪዎቹን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ከማድረግ ባለፈ የከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም አቶ አለሙ ተናግረዋል።

በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኘውን ስፋቱ 115 ሺህ 500 ሜትር ስኩዌር የሆነውን ስታዲየም ዙሪያ 1 ሺህ 360 ሜትር አጥር በ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር መገንባቱንም ገልጸዋል።

ከ860 ሚሊዮን ብር በላይ ለሚጠይቀው የወልቂጤ ጠቅላላ ሆስፒታል የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ከቴሌቶን ገቢ 22 ነጥብ 3 ሚሊዮን ጥሬ ገንዘብ፣ 11 ሚሊዮን ብር በዓይነት እና ከጤና ሚኒስቴር 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በአጠቃላይ 53 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

ማህበሩ የሆስፒታሉን ግንባታ ፕሮጀክት ለዞኑ በማስረከቡና ዞኑም ለወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አስረክቦ በአሁኑ ወቅት ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በቴሌቶኑ 10 ሚሊዮን ብር ለማበርከት ቃል የገቡት የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ቃል በገቡት መሰረት አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት ማስገንባታቸውንም ጠቁመዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎ ያደረገበት የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን መርሃ ግብር 150 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታልሞ የተከናወነ ሲሆን በወቅቱ 231 ሚሊዮን 721 ሺህ 752 ብር ለመለገስ ቃል ተገብቶ ነበር።

ቃል ከተገባው ውስጥ 67 በመቶ ያህሉ ተሰብስቦ ለልማት መዋሉን ከማህበሩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም