በአትናጎ በግብርና ቴክኖሎጂና በገበያ ትስስር ላይ ያተኮረ ዐውደ ርዕይ በጅማ ከተማ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በአትናጎ በግብርና ቴክኖሎጂና በገበያ ትስስር ላይ ያተኮረ ዐውደ ርዕይ በጅማ ከተማ ተካሄደ
ጅማ መጋቢት 29/2011 አርሶ አደሩን ከግብርና ቴክኖሎጂ ጋር ያስተዋወቀና በገበያ ትስስር ላይ ያተኮረ ዐውደ ርዕይ በጅማ ዞን አትናጎ ከተማ ተካሄደ፡፡
በዐውደ ርዕዩ ከ3ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተሳትፈውበታል፡፡
ዐውደር ዕዩን ያዘጋጀው ''ፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ ቫልዩ ቼን አክቲቪቲ'' የተሰኘ የአሜሪካ ዓለምአቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት አካል ነው፡፡
የድርጅቱ የቡና ሰንሰለት አማካሪ አቶ ክልል መስፍን ለኢ ዜ አ እንደገለጹት ዐውደ ርዕዩ ድርጅታቸው ዐውደ ርዕዩ በወረዳ ደረጃ አርሶ አደሮችን ከዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂ ጋር የሚያስተዋወቅና የገበያ ትስስር ፈጥሯል።
ለአርሶ አደሮቹ የእርሻ መሣሪያዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርቦለቸው መግዛታቸውን ተናግረዋል ፡፡
ድርጅቱ ስድስት እሴት የተጨመረባቸው የግብርና ምርቶችን ለገበያ በማቅረብና የገበያ ትስስር በመፍጠር 300 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡እስካሁንም የእቅዱን 50 በመቶ አሳክቷል ብለዋል፡፡
ሰንሰለት እንዲፈጠርላቸው የተመረጡት የቡና ልማት ፣እንስሳት ማደለብ፣ የሽንብራ ልማት፣ የወተት ምርት ፣በቆሎና የዶሮ እርባታ ናቸው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ምርታማነትና ግብይት ባለሙያ አቶ አበበ ሚጀና ለሊሙሰቃና አካባቢው አርሶአደሮች የምርት ሂደታቸውን ቀላል የሚያደርጉና ጉልበት የሚቆጥቡ የእርሻ መሳሪያዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
ዐውደ ርዕዩን ''አርሶ አደሮች የተሻለ አምርተው፤ የተሻለ ገበያ የሚያገኙበት'' ብለውታል።
በዐውደ ርዕዩ ከካልቤ የእርሻ መሣሪያዎች አስመጪ ድርጅት የተሳተፉት አቶ ደስታ ፍቃዱ ለጎብኚዎች የበቆሎ መፈልፈያ መሣሪያ እያስተዋወቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
መሣሪያው በሰው ኃይል በሰዓት 25 ኩንታል፣በሰው ኃይል ሲሰራ ደግሞ በሰዓት እስከ ስድስት ኩንታል የበቆሎን ፍሬ ከቆረቆዳው ይለያል ብለዋል፡፡
አርሶ አደር ጀማል ሼህ አባሉሌሳ በዐውደ ርዕዩ የተሳተፉ አርሶ አደሮች አዳዲስ ነገሮችን በማየት የሚማሩበትና ለቀጣይ ሥራቸው መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
ወጣት ኤልያስ አበበ በበኩሉ ''ዐውደ ርዕዩ ለአርሶ አደሩ የእርሻ ሥራ ዕወቅና የሚሰጥና ግንዛቤውን የሚያሳድግ ነው'' ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎችና ግብዓት አቅራቢ ድርጅቶች ከአርሶ አደሩ ጋር በአካል መገናኘታቸው ለገበያ ትስስርም ያግዛል ብሏል፡፡
በዐውደ ርዕዩ ላይ 60 የሚደርሱ ዩኒዬኖች፣የግብርና ኅብረት ሥራ ማህበራት፣ባለሀብቶች፣የግብርና ምርምር ተቋማትና አግባብ ያላቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡
አትናጎ የሊሙ ሰቃ ወረዳ ዋና ከተማ ናት።