ከወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ ብድር የወሰዱ 140 ኢንተርፕራይዞች በስራ ላይ የሉም ተባለ

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2011 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር የወሰዱ 140 ኢንተርፕራይዞች በስራ ላይ እንዳልተገኙ የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ገለጸ።

በአገር አቀፍ ደረጃ በ2009 ዓ.ም ለወጣቶች ስራ ፈጠራ የሚውል 10 ቢሊዮን ብር ለተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ መንግስት መመደቡ የሚታወስ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 419 ሚሊዮን ብር ለአዲስ አበባ ከተማ የተመደበ ነው።

ብድሩን የሚሰጠውና የሚያስመልሰው የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብድሩን በወሰዱ ኢንተርፕራይዞች ላይ ባደረገው ክትትል የተወሰኑት በስራ ላይ እንዳልተገኙ አረጋግጧል።

በተቋሙ የማርኬቲንግና ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ መስፍን ፊጡማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በከተማዋ እስከ የካቲት 2011 ዓ.ም ድረስ 2 ሺህ 116 ኢንተርፕራይዞች ብድር ወስደዋል።

እንደ ሃላፊው ገለጻ፤ ከ17 ሺህ በላይ አባላት ያሏቸው እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ለከተማዋ ከተፈቀደው 419 ሚሊዮን ብር ብድር ወስደዋል።

ተቋሙ ለከተማዋ የተመደበውን ፈንድ እስከ ባለፉት ስድስት ወራት ሙሉ ለሙሉ አበድሮ ማጠናቀቁን የገለጹት ሃላፊው ከተመለሰው ብድር ተጨማሪ 21 ሚሊዮን ብር በመስጠት ባጠቃላይ 440 ሚሊዮን ብር ብድር መሰጠቱን ተናግረዋል።

ተደራጅተው ብድር ከወሰዱት መካከል 140 ኢንተርፕራይዞች መመለስ የሚገባቸውን 24 ሚሊዮን ብር ይዘው በስራ ገበታቸው ላይ አልተገኙም።

ብድሩን የወሰዱ ወጣቶች አብዛኞቹ ሙያተኞች በመሆናቸው ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ ማመቻቸትና ሰርተው እንዲመልሱ ማድረግ ካልሆነ የወሰዱትን ብድር እንዲመልሱ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢንተርፕራይዞች ብድሩ ከተፈቀደ ጀምሮ የወሰዱ ሲሆኑ በግንባታ፣ በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፍ የተደራጁ ወጣቶች ናቸው።

ኢንተርፕራይዞች ብድር የሚመልሱበት ጊዜ እንደተሰማሩበት የስራ መስክ የሚወስነው ሲሆን  እስከ 4 አመት ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል።

ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ ከተሰጠው 419 ሚሊዮን ብር ብድር ውስጥ 157 ሚሊዮን ብር ተመላሽ ተደርጓል።

ተደራጅተው ወደ ስራ ለመግባት ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ብድሩን ለማግኘት ቅድሚያ 20 በመቶ መቆጠብ እንደሚጠበቅባቸው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር አላማ አድርጎ የተመደበው 10 ቢሊዮን ብር እስከ ባለፉት ስድስት ወራት አብዛኞቹ ክልሎች የተመደበላቸውን ገንዘብ እንደተጠቀሙ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም