ቀጥታ፡

ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱሰትሪ የምርት ጥራት መረጋጋጥ የካይዘን አሰራር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ

አዳማ መጋቢት 28/2011  የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን የምርታማነት ጥራትና ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ውስጥ የካይዘን አሰራር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የካይዘን የአሰራር ፍልስፍና ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርምና እድገት በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ዓመታዊ የምክክር መድሬክ ዛሬ  በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል።

በመድረኩ የኢንስቲትዩቱ  ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ደመቀ " በሀገራችን በምርታማነት ላይ የሚስተዋለውን  የጥራት፣የጊዜ፣የሀብትና የሰው ሃይል ብክነት ችግሮችን ለማስወገድ የካይዘን ፍልስፍና ወሳኝ ሚና አለው "ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በተመረጡ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ካይዘን እንዲተገበሩ በማድረግ ከ76 ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ ከብክነት ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

ቀደም ሲልም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከ700 በላይ በሚሆኑት አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የካይዘን አመራርና የአሰራር ፍልስፍናን ተግባራዊ በማድረግ ከ2 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መዳኑንም አመላክተዋል።

ሀገሪቱ ካይዘን በመተግበሯ በጃፓን መንግስት የአፍሪካ የካይዘን ልህቀት ማእከል ሆና መመረጡዋን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ለልህቀት ማዕከል ግንባታ የጃፓን መንግስት የገንዘብ  ድጋፍ ማድርጉን ጠቁመዋል።

ኢኒስቲትዩቱ ከአዲስ አበባ መስተዳደር በተረከበው ቦታ ላይ የማዕከሉን ግንባታ ለማስጀመር  ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከ50  በላይ አማካሪዎችና ተመራማሪዎችን በካይዘን አመራር ፍልስፍና በማስተማር ወደ ጥናትና ምርምር ሥራ እንዲገቡ ማድረጋቸው ጠቅሰው በተጨማሪው 26 ተማሪዎች በድህረ ምረቃ እያስተማሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የሲቪል ሰርቨስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ ፈይሳ በበኩላቸው " የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን የምርታማነት ጥራትና ተዳዳሪነት ለማረጋገጥ ካይዘን አንዱ ሀገራዊ የሪፎርም መሳሪያ ነው "ብለዋል።

ሀገራዊ የምርታማነት ጥራት ንቅናቄ ትኩረት በተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች በማስጀመር የማኑፋክቸሪንግ ምርቱን የተወዳዳሪነት አቅም ለማጎልበት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የካይዘን ኢንስቲትዩቱ የማማከር፣የጥራት ምዘናና እውቀና ለተቋማት በመስጠት ተወዳዳሪነት ከማሳደግ አንፃር በርካታ ተግባራት ማከናወኑ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ የተጀመረው የኢኮኖሚ ሪፎርምና እድገት በካይዘን አሰራርና አመራር ፍልስፍና ለመደገፍ መድረኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የምክክር መድረኩ  የኢንስቲትዩቱ አማካሪዎች፣ተመራማሪዎች፣በዘርፉ የሚሰሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ምሁራን የጥናና ምርምር ጽሑፎች እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም