ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን በኦሎምፒክ ማጣሪያው ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዞን የኦሎምፒክ ማጣሪያ የኡጋንዳ አቻውን በድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ።

ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ በካምፓላ ስታር ታይምስ ስታዲየም ባደረገው የመልስ ጨዋታ ሎዛ አበራ በ66ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ብቸኛ ግብ የኡጋንዳ ሴቶች አሎምፒክ ብሔራዊ ቡድንን ማሸነፍ ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎም የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን በድምር ውጤት 4 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 3 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የቀጣይ ዙር ጨዋታውን ከካሜሮን አቻው ጋር በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም የሚያደርግ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ በሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ለመሳተፍ ነው።

አፍሪካ በኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድሩ በሴቶች ሁለት ብሔራዊ ቡድኖችን የማሳተፍ ኮታ አላት።

በወንዶቹ የአፍሪካ ዞን ኦሎምፒክ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሔራዊ በያዝነው መጋቢት አጋማሽ ከማሊ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ በድምር ውጤት 5 ለ 1 ተሸንፎ ከውድድሩ በመጀመሪያ ዙር መሰናበቱ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በኦሎምፒክ ጨዋታዎች በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በተለይም በአትሌቲክሱ ብዙ ታሪክ ብታስመዘግብም በእግር ኳስ ግን ተሳትፋ አታውቅም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም