ኦዴፓ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተከባብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ይታገላል - አቶ ለማ መገርሳ - ኢዜአ አማርኛ
ኦዴፓ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተከባብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ይታገላል - አቶ ለማ መገርሳ
አዲስ አበባ መጋቢት 28/2011 የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተከባብረው የሚኖሩባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ይታገላል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንትና የኦዴፓ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ለማ መገርሳ ተናገሩ።
ፓርቲው የተመሰረተበት 29ኛ ዓመት በሚሊኒየም አዳራሽ እየተከበረ ይገኛል።
አቶ ለማ መገርሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ባለፈው አንድ ዓመት የታየው ለውጥና ድል የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያዊ በጋራ ያመጣው ለውጥና ድል ነው።
የኦሮሞ ህዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥሎ የሚታይ እንዳልሆነና የኢትዮጵያ ትልቁ አካል እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ለኦሮሚያ ህዝብ መታገል ማለት የኦሮሞ ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት መታገል ማለት እንደሆነም ነው አቶ ለማ ያስረዱት።
ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነት አንድ ሆነውና ተከባበረው በሰላም የሚኖሩባትን አዲሲቷ ኢትዮጵያን ለመፍጠርና ለህዝቡ አንድነት፣ ክብርና ሰላም ኦዴፓ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትግል ያደርጋል ብለዋል አቶ ለማ።
"በጋራ ተባበረን አሁን ላለንበት ደረጃ እንደደረስን ሁሉ ከፊታችን ያለውን የድህነት ተራራ ለመናድ በጋራ ተባብረንና ተመካክረን መስራት አለብን" ብለዋል።
"አሁን ያለውን የድህነት ብርድ ለማጥፋት ነጠላ ሳይሆን ጋቢ መልበስ አለብን" ያሉት አቶ ለማ "እኛ ብቻችንን ነጠላዎች ሆነን ድህንነትን ማሸነፍ ስለማይቻል ጋቢ በመልበስ በጋራ በመተባባር መስራት ይገባናል" ሲሉ ተናግረዋል።
ሁሉንም የምታከብርና የምታስከብር አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ሁሉም በጋራ መታገል እንደሚገባውም አሳስበዋል።
በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 29ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ እህትና አጋር ፓርቲዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ደጋፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።