ቀጥታ፡

የቀርከሃ ረቂቅ ስትራቴጅክ የልማት እቅድና የድርጊት መረሃ ግብር ተዘጋጀ

አዳማ መጋቢት 28/2011 የቀርከሃ ሀብት በሀገሪቱ ልማትና እድገት ውስጥ ተገቢውን ሚና እንዲኖረው ለማስቻል ረቂቅ  ስትራቴጅክ የልማት እቅድና የድርጊት መረሃ ግብር ማዘጋጀቱን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ስለዚሁ እቅድና መረሃ ግብር ግንዛቤ ለማስጨበጥ  ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ አካሄዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ከበደ ይማም እንደገለጹት የተጋዘጀው ረቂቅ  ስትራቴጅክ የልማት እቅድና የድርጊት መረሃ ግብር ሀገሪቱ ከቀርከሃ ሀብት ልማት ተገቢውን ጥቅም እንዲታገኝ ለማስቻል ነው፡፡

" በሀገራችን  ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለቀርከሃ ሀብት ልማት የሚውል አቅም አለ"  ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ እስከ አሁን በሰው እና  በተፈጥሮ ከአንድ ሚሊዮን 400 ሺህ   ሄክታር በላይ መሬት በቀርከሃ ደን መሸፈኑን ተናግረዋል።

እቅዱና የድርጊት መረሃ ግብሩ  በአጭርና በረዥም ጊዜ በመከፋፈል ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ቀርከሃን በማልማት በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት  እድገት ውስጥ የጎላ ሚና ይኖረዋል።

ከ2011 እስከ 2015 በስትራቴጅክ እቅድ አሁን ከላው የቀርከሃ ደን በተጨማሪ 100ሺህ ሄክታር ተጨማሪ ለማልማትና ከ30 ሚሊዮን ቶን በላይ የካርበን ልቀት ለመቀነስ ግብ መቀመጡን አመልክተዋል።

በዘርፉ ከ600ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ  የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን በብዛት በማሳተፍ  የምርት ውጤቶችን ለዓለም ገበያ በስፋት ለማቅረብ  ጭምር እንደሆነ  አቶ ከበደ አስረድተዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማድረስና ከውጭ  የሚገባውን የእንጨት ውጤቶች በሀገር ውስጥ  ለመተካትም እንዲሁ።

" በ2021 ዓ.ም ደግሞ የቀርከሃ ደን ልማት ወደ 3 ሚሊዮን ሄክታር ለማሳደግ ግብ አስቀምጠናል"  ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ሚንዛሪ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግም ነው" ብለዋል።

ረቂቅ ስትራቴጅክ የልማት እቅድና የድርጊት መረሃ ግብሩ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በቀርከሃ ደን እንዲሸፉኑ ከማድረግ አንፃር ፋይዳው የላቀ ነው ተብሏል፡፡

" ሀገሪቱ በቀርከሃ ሀብት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ብትይዝም እስካሁነ ከዘርፉ እያገኘች ያለው ጥቅም እዚህ ግባ የሚበል አይደለም "ያሉት ደግሞ በኮሚሽኑ ከፍተኛ የደን ባለሙያ የሆኑት አቶ አሸብር ወንድሙ ናቸው።

ስትራቴጅክ እቅዱ ቀርከሃ  የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን መቋቋም በሚችልበት መልኩ ለማልማትና ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የተቀረፀ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ በቀረቡት ጥናታዊ ፁሑፍ እንደተመለከተው በሀገሪቱ የቀርከሃ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው በባህላዊ መንገድ በመሆኑ እየተገኘ ያለው ጥቅም ዝቅተኛ ነው።

እስካሁን  ሦስት ባለሃብቶች ብቻ በዘርፉ መሰማራታቸውንና  ሀብቱ በሚፈለገው መልኩ አገልግሎት እንዳይሰጥ ያደረገው ዘርፉ የሚመራበት ስትራቴጅና የማስፈፀሚያ ስልቶች ባለመኖራቸው እንደሆነ ተመልክቷል።

አሁን የተዘጋጀው ስትራቴጂ በመንግስት ይዞታነት ሥር ከሚገኘውና ከሚለማው በተጨማሪ የቀርከሃን ደን በአርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች እንዲሁም በግል ባለሃብቶች ከ200ሺሀ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ጭምር የታቀደ ነው፡፡

የቀርከሃ  ረቂቅ ስትራቴጅክ የልማት እቅድና የድርጊት መረሃ ግብር ከተያዘው የበጀት ዓመት ጀምሮ በሁለት ምዕራፍ ለቀጣዩ አስር ዓመታት የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም