የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀሌ ከአንድ ቢለዮን ብር በሚልቅ ወጪ ዘመናዊ ህንጻ እያስገነባ ነው

178

መቀሌ መጋቢት 28/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  እጨመረ የመጣውን  የተገልጋይ ብዛትና ፍላጎት ለማርካት  የሚያግዝ  ዘመናዊ ህንጻ ከአንድ ቢሊዮን ብር በሚልቅ ወጪ በመቀሌ ከተማ እያስገነባ ነው፡፡

ህንጻው  17 ወለል ያለው መሆኑን በባንኩ የመቀሌ ዲስትሪክት  የህንፃ ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ አካለይ ተክላይ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ዮቴክ በተባለ ሀገር በቀል ህንጻ ተቋራጭ እየተገነባ ያለውን ዘመናዊ የንግድ ባንክ ህንጻ በ900 የስራ ቀናት ግንባታ ለማጠናቀቅ ነው ውል የተገባው፡፡

በተያዘው ዓመት ጥቅምት ወር ግንባታው የተጀመረው የባንኩ ዘመናዊ ህንጻ  በመቀሌ ዲስትሪክት እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ብዛትና ፍላጎት ለማስተናገድ እንደሚያግዝ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

የተቋራጩ ምክትል ስራ አስከያጅ አቶ ሰሎሞን ዘፈሩ በበኩላቸው በገቡት ውል መሰረት  አጠናቅቀው ለማስረከብ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ህንፃው በ2ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የሚያርፍና አሁን የመሰረት ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክተው በስራው ሂደት እስከ 400 ለሚሆኑ ባለሙያዎችና የጉልበት ሰራተኞች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት አንድ ሚለዮን 300ሺህ የነበረው የተገልጋዮች ቁጥር አሁን በ100ሺህ ጭማሪ ማሳየቱን የተናገሩት ደግሞ በዲስትሪክቱ  የኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ሀጎስ ናቸው፡፡

በመቀሌ  እየተሰራ ያለው ባለ17 ወለል ህንፃ ተጠናቆ  አገልግሎት ሲጀምር የተገልጋዮች ብዛትና ፍላጎት በተሟላ መንገድ ለመቀበል  እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል፡፡

ንግድ ባንክ በትግራይ ክልል ከሉት ከ105 ቅርንጫፎች ውስጥ በረሱ ህንጻ ሆኖ አገልግሎት የሚሰጥባቸው በ10 ቅርንጫፎች ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊ  አቶ ሃፍቶም ፋንታሁን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀሌ እያስገነባ ያለው ዘመናዊ ህንጻ  ወደ ውጭ ለሚላኩና ለሚገቡ እቃዎች የፋይናንስ ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል የክልሉ ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ  የተሰማሩ ባለሀብቶች የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዙ የጠቀሱት ኃላፊው  ህንጻው ሲጠናቀቅ በአቅራቢያቸው አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቀሌ ዲስትሪክት የተፋጠነ አገልግሎት እየሰጣቸው እንዳልሆነ ተገልጋዮች ቅሬታ እንዳሳደረባቸው መግለጻቸውን  ኢዜአ  ከሳምንት በፊት  ዘግቦ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም