ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ቀደም ብለው የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃን በስነ-ህይወታዊ ዘዴ የማጠናከር ስራ ተጀመረ

ባሀርዳር ግንቦት 25/2010 በአማራ ክልል በበጋ ወራት የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባር በስነ-ህይወታዊ ዘዴ የማጠናከር ስራ መጀመሩ ተገለጸ፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ እንዳመለከተው የማጠናከሩ ሰራ የተጀመረው ከስድስት ሺህ 700 በሚበልጡ ተፋሰሶች ላይ ነው፡፡ በቢሮው የስነ-ህይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥምር እርሻ ደን ባለሙያ አቶ እስመላለም ምህረቱ እንደገለጹት በተፋሰሶቹ ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ተከናውኗል። በአርሶ አደሩ ተሳትፎ ከጥር 1 እስከ መጋቢት 20/2010 ዓ.ም ድረስ ከተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ መካከል የማሳና የጋራ ላይ ዕርከንና የቦረቦር ልማት ስራዎች ይገኝበታል። እንዲሁም 22 ሚሊዮን የተለያዩ የውሃ ማስረጊያ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን ተራቁቶ የነበረ ስፋት ያለው መሬትም በመከለል ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ እንዲጠበቅ ተደርጓል። የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተፋሰስ ራስጌ በመሆኑ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ  በስነ-ይውወታዊ የማጠናከሩ ስራ መጀመሩን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ ቀድሞ ዝናብ መጣል በጀመረባቸው የክልሉ ደጋማ አካባቢዎች እስካሁን 618 ኩንታል የተለያዩ የሳር ዝርያዎችን ቀርበው በማሳ ላይ በተሰሩ ዕርከኖች ላይ መዝራት ተጀምሯል። አሁን የጀመረው ዝናብ ሳያቆራርጥ ከቀጠለም ከቀጣዩ ወር አጋማሽ ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብት የተሰራባቸውና በሌሎች ቦታዎች የሚተከሉ ከ1 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል። " በበጋ ወራት በዘመቻ የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት በስነ-ህይወታዊ ዘዴ ማጠከር ጀምረናል"  ያሉት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ የመሶበ ተራራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለምነው ውቤ ናቸው። ከዚህ በፊት ያከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የአፈር ለምነቱ በመመለሱ በፊት እስከ 35 ኩንታል በሄክታር ያገኙት የነበረውን የድንች ምርት አሁን ከሶስት እጥፍ በላይ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ካገገሙ ተፋሰሶችም ለእንስሳት በቂ መኖ እያገኙ መሆነቸውን የጠቀሱት አርሶ አደሩ፤ ይህም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች በባለቤትነት እየጠበቁ በቀጣይም ችግኝ በመትከል የመንከባከብ ስራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል። የተፈጥሮ ሃብት መስራት ሳይጀምሩ ከሩብ ሄክታር መሬት ከስድስት ኩንታል ያልበለጠ የቢራ ገብስ ምርት ያገኙ እንደነበርና አሁን ወደ11 ኩንታል እንዲያድግ እንዳስቻላቸው የገለጹት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የቀበሌ አንድ አርሶ አደር ጌጤ አስማማው ናቸው፡፡ ዘንድሮም በበጋ ወራት ያከናወኑትን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በስነ-ህይወታዊ ዘዴ ለማጠናከር መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል። በክልሉ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በህዝብ ንቅናቄ በተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ከስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት አገግሞ ወደነበረበት መመለሱን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም