ቀጥታ፡

ቻይና በአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎቿ የመታሰቢያ መርሃ ግብር አካሄደች

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2011 በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ስምንት ቻይናዊያን የመታሰቢያ መርሃ ግብር አካሄደ።

አደጋው በተከሰተበት ሥፍራ በተካሄደው መርሃ ግብር የኤምበሲው ሠራተኞች የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ቻይናዊያን  እንፀልያለን ብለዋል።

ለሟች ቤተሰቦችም ልባዊ መፅናናትን እንመኛለን በማለት ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ቢሾፍቱ አካባቢ መከስከሱ ይታወሳል።

በአደጋው 149 መንገደኞችና ስምንት የበረራ ሠራተኞች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በቅርቡም የአውሮፕላኑ የመረጃ ሣጥን /ብላክ ቦክስ/ በፈረንሳይ አገር ከተመረመረ በኋላ የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ሥሪት ላይ ችግር መኖሩ ተረጋግጧል።

የቦይንግ ኩባንያም በመርማሪ ቡድኑ የወጣውን መረጃ በመቀበል ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ይቅርታ ጠይቆ ለሟቾች ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝቷል።

ያም ሆኖ የመረጃ ሣጥኑ ሙሉ መረጃ ወደፊት የሚገለጽ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም