ምክር ቤቱ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ
አዲስ አበባ መጋቢት 27/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው ልዩ ስብስባ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።
ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይትና ክርክር በማካሄድ በአብላጫ ድምጽና በአንድ ድምጽ ተአቅቦ ረቂቁ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 ሆኖ እንዲጸድቅ ወስኗል።
የምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንደገለጹት መንግስት በአገሪቷ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።
በዚህም ከምርጫ ቦርድ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ህጎች የማሻሻል፣ ህብረተሰቡና ተፎካካሪ ፓሪቲዎችን ሊያስማማ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እያዘጋጀ ሲሆን የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
አዋጁ ምርጫ ቦርዱ ገለልተኛና ተአማኒ ሆኖ እንዲቋቋም፣ የምርጫ ቦርድ አባላት ከብቃትና ስነ ምግባር ባሻገር በተቻለ መጠን የብሔርና የጾታ እኩልነትን ያማከሉ እንዲሆኑ ያስችላል።
የምርጫ ቦርድ አባላት ኢትዮጵያዊ መሆን እንዳለባቸው አዋጁ የሚያስገድድና የውጭ አገር ዜጋ በህግ የኢትዮጵያ ዜግነት አግኝቶ የምርጫ ቦርድ አባል እንዳይሆን እንደሚያግድ ገልጸዋል።
አዋጁ ተሻሽሎ መቅረቡ ጠንካራ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም ለማደረጃት፣ ለቦርዱ የሚመደቡ አባላት የሚመለመሉበትና የሚሾሙበት አስራር ግልጽ እንዲሆን፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ነፃነትና ገለልተኛነትን ለማረጋገጥ ያስችላል።
በተለይም በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አደረጃጀት እንዲኖር ለማድረግ አዋጁ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ሲሉ አብራርተዋል።
የምርጫ ቦርድ አባላት የአገልግሎት ጊዜያቸው ሁለት ዓመት ሆኖ የስራ ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲለቁ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ በማንኛውም የመንግስት የስራ ኃላፊነት ቦታ ላይ እንዳይሾሙም ያደርጋል።
ምክር ቤቱ ማብራሪያውን ካደመጠና ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 ሆኖ እንዲፀድቅ በአብላጫ ድምጽ ወስኗል።