ሚኒስቴሩ ግድቡን ለቱሪዝም ለማዋል ከወዲሁ ትኩረት እንዲሰጥ ጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ ግድቡን ለቱሪዝም ለማዋል ከወዲሁ ትኩረት እንዲሰጥ ጠየቀ
አሶሳ መጋቢት 27/2011 የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር አካባቢውን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል ከወዲሁ ትኩረት እንዲሰጠው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጠየቀ፡፡
በሆቴል አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ስልጠና ዛሬ በአሶሳ ተካሂዷል፡፡
በሚኒስቴሩ የቱሪስት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጫና ምደባ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው በዚህ ጊዜ እንዳሉት ግድቡን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡
ግድቡን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ሥራው ከግንባታው በተጓዳኝ መከናወን እንደሚኖርበት ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፣ለዚህም የፌዴራልና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግሥታት ትኩረት እንዲሰጡት ጠቁመዋል፡፡
በግድቡ የሚከናወን ግንባታ የመሠረተ ልማት ተቋማትን እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታልም ብለዋል፡፡
ግድቡ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት እንደመሆኑና በአገር ውስጥና በውጭ ዜጎች ከመጎብኘቱ አኳያ በመስህብነት ያዳበረውን ልምድ እንዲጠቀምበት አቶ ቴዎድሮስ መክረዋል፡፡
አሶሳ ባላት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና በከተማው እየተበራከቱ የመጡት ሆቴሎችም በግድቡ ላይ ለሚካሄደው እንቅስቃሴ አመቺ እንደሚያደርጉም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በቀጣይም የአገሪቱን የቱሪዝም ፍኖተ ካርታን መሠረት በማድረግ ድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አስካለ ተሰማ ቢሮው የቱሪስት መስህቦችን ለመጨመርና ሆቴሎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጡበትን አቅም ለመገንባት ጥረቱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
በስልጠናው 50 የሚጠጉ የሆቴል ባለቤቶች ተሳትፈዋል፡፡
ግንባታው ከተጀመረ ስምንት ዓመታት የሞላው የህዳሴው ግድብ ግንባታ እስካሁን 66 ከመቶ ተከናውኗል።
በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ግንባታውም ተጠናቅቆ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት 150 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ መገለጹ ይታወሳል።
ግድቡ ከውጥኑ ጀምሮ የቱሪስት መስህብ እንደሚሆን ሲነገር እንደነበርም አይዘነጋም።