ቀጥታ፡

ወላይታ ድቻ በአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር ሁለተኛ ድሉን አስመዘገበ

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2011 ወላይታ ድቻ ካይሮ ላይ እየተካሄደ ባለው በአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር ሁለተኛ ድሉን አስመዘገበ።

በምድብ አራት የሚገኘው ወላይታ ድቻ ዛሬ በምድቡ አራተኛ ጨዋታውን ከብሩንዲው ሩኪንዞ ክለብ ጋር አድርጎ በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ወላይታ ድቻ ጨዋታውን ያሸነፈው ከሁለት ለዜሮ መመራት ተነስቶ እንደሆነ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሉ ጨዋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ወላይታ ድቻ ነጥቡንም ወደ ስድስት በማሳደግ በምድቡ ከነበረበት አምስተኛ ደረጃ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

የወላይታ ድቻ የዛሬው ድል የኢትዮጵያን የቮሊቦል አፍቃሪ ያኮራ ነው ሲል የአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን በድረ ገጹ አስፍሯል።

ክለቡ ነገ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታውን ከካሜሮኑ ፋፕ ክለብ ጋር የሚያደርግ ሲሆን ጨዋታውን ካሸነፈ ወደ ሩብ ፍጻሜ የማለፍ ዕድል ይኖረዋል።

ወላይታ ድቻ ከዛሬው ድል በኋላ ለነገው ጨዋታ ልምምድ ማድረግ መጀመሩንና የተጫዋቾቹ የቡድን መንፈስ ጠንካራ መሆኑን አቶ ተክሉ ተናግረዋል።

በአፍሪካ የቮሊቦል ውድድሮች በተደጋጋሚ በመሳተፍ ልምድ ያገኘው ወላይታ ድቻ በዘንድሮው የክለቦች ውድድር ከተሳታፊነት ወደ ውጤታማነት ያሸጋገረውን ድል እያስመዘገበ እንደሆነም አመልክተዋል።

ክለቡ ያስመዘገባቸው ድሎች ለኢትዮጵያ ቮሊቦል ዕድገት መነቃቂያ ይሆናልም ብለዋል።

በምድብ አንድ የሚገኘው ሙገር ሲሚንቶ ነገ ካለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ከግብጹ አል ሀሊ ክለብ ጋር የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ያደርጋል።

ክለቡ እስካሁን ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።

38ኛው የቮሊቦል ክለቦች ውድድር እስከ ሚያዚያ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም