በአማራ ክልል የሕገ-ወጥ ነጋዴዎች መበራከት ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከውድድር ውጭ እያደረጋቸው ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የሕገ-ወጥ ነጋዴዎች መበራከት ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከውድድር ውጭ እያደረጋቸው ነው
ባህርዳር መጋቢት 27/2011 በአማራ ክልል የሕገ-ወጥ ነጋዴዎች መበራከት ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከውድድር ውጭ እያደረጋቸው መሆኑን የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ገለጹ።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሕዝብ ክንፍ የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የንግድና ዘርፍ ማህበራት አመራሮች እንደገለጹት በክልሉ የሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ቁጥር መበራከት በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱት ነጋዴዎችን ሕልውና አደጋ ላይ ጥሎታል።
የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ዋና ፀሐፊ አቶ ንብረት ባንተ ይገኝ በክልሉ ያለ ንግድ ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ቁጥር መጨመር
በሕጋዊ መንገድና ግብር ከፍለው የሚሰሩ ነጋዴዎችን እንቅስቃሴ ውሱን እንዳደረገው ይናገራሉ።
ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ መሥመር ማምጣት ካልተቻለ፤ የክልሉን የንግድ እንቅስቃሴ እየጎዳው መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባዋል ያሉት የባህር ዳር ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ቦርድ አባል አቶ መኮንን ዓለሙ ናቸው።
በሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ ካልተወሰደ፤ሕጋዊ ነጋዴዎችን እንቅስቃሴ ከማቀጨጭ በላይ፤የክልሉን የንግድ ገቢ እንዲያሽቆለቁል ማድረጉን አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ ከአገራዊ ለውጥ ጋር ተያይዞ በክልሉ ሕገ ወጥ ንግድ መንሰራፋቱን ያምናሉ።
ቢሮው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ42 ሺህ ነጋዴዎች በላይ የንግድ ፈቃድ እንደሰረዘም ገልጸዋል።
ከመካከላቸውም 682 የሚደርሱ ነጋዴዎች በእሥራትና በገንዘብ ተቀጥተዋል።
አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት ተወርሶባቸው ለመንግሥት ገቢ መደረጉንም ተናግረዋል።
ቢሮው ሕግን-የማስከበር ሥራውን እንደሚያጠናክር የገለጹት አቶ ተዋቸው፣ኅብረተሰቡም ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን በመጠቆም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል 419 ሺህ ሕጋዊ ነጋዴዎች እንደሚገኙ ከክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።