የወይዘሪት ናዝራዊት አበራን ጉዳይ መንግሥት በቅርበት እየተከታተለው ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

88

አዲስ አበባ  መጋቢት 27/2011 በቻይና እስር ቤት የምትገኘውን የወይዘሪት ናዝራዊት አበራ ጉዳይ መንግሥት በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ መንግሥት የወይዘሪት ናዝራዊት አበራን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለው ነው ብለዋል።

የዋና መሥሪያ ቤት የኤዥያና የፓስፊክ ጉዳዮች ጄኔራል ዳይሬክተርና በቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳዩን እየተከታተለው መሆኑን ገልጸዋል።

ጉዋንዡ የሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ከቻይና መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በመሆን በእስር ላይ ሠብዓዊ መብቷ እንዳይጣስ ማድረጉን አንስተዋል።

በሕጋዊ መልኩ ራሷን እንድትከላከል ድጋፍ እየተሰጣት መሆኑንና እስካሁንም ሦስት ጊዜ መጎብኘቷን ጠቅሰዋል።

በቀጣዩ ሳምንት ለአራተኛ ጊዜ እንደምትጎበኝም ነው ቃል አቀባዩ ያስታወቁት። 

ወይዘሪት ናዝራዊት እስካሁን በወንጀል ተጠርጥራ በእስር ላይ ትገኝ እንጂ ምንም አይነት የፍርድ ውሳኔ እንዳልተላለፈባትም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

የቻይና መንግሥት አቃቤ ሕግ ክስ እንዳልመሰረተባትም አስረድተዋል።

በመሆኑም በማኅበራዊ ሚዲያ በወይዘሪት ናዝራዊት ላይ ውሳኔ ተላልፎባታል ተብሎ የሚናፈሰው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በሌላ ዜና በዚህ ሣምንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአርሜኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዞህራብ መናተሳ ካናያን ፍሬያማ ቆይታ እንደነበራቸው አቶ ነብያት ገልጸዋል።   

በኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የልህቀት ማዕከላት ለመገንባትና ኤምባሲ ለመክፈት ፍለጎት እንዳላቸው መግለጻቸውንም ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተዘጋጀው "ሸገር እራት" መርኃ ግብር ኤምባሲዎች እንዲሳተፉ የማስተዋወቅ ሥራ መሠራቱንም አክለዋል።                                                                        

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም