በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል - ምሁራን
አዲስ አበባ መጋቢት 27/2011 የአገር ህልውናን የሚፈታተኑና በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮችን ለማስቆም መንግስት በአፋጣኝ የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር ምሁራን ሃሳብ አቀረቡ።
ምሁራኑ መንግስት የጥላቻ ንግግሮች እንዲቆሙ ቢያስጠነቅቅም እየተባባሱ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የጨመረ ሲሆን ለበጎ ዓላማ የተፈጠረው ቴክኖሎጂም ለመከፋፈል፣ ለሰላምና ፀጥታ መደፍረስ መንስኤ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በማህበራዊ ሚዲያ የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮች ለአገር አንድነትና ለዜጎች ተከባብሮ መኖር ስጋት ከሆኑም ውሎ አድሯል።
ለኢዜአ አስተያየታቸው የሰጡ ምሁራን እንደገለፁት በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች መነሻቸውን ያደረጉት በፖለቲካ ሳቢያ በተፈጠሩ ብሶቶች እንደሆነ ያስረዳሉ።
የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ግደይ ደገፉ ይህ ብሶት አድጎ ወደ ማህበራዊ ሚዲያው መምጣት፣ ያለገደብ መነገርና መባባስ ደግሞ የአገር ህልውናን እየፈተነ ነው ይላሉ።
የጥላቻ ንግግሮች አሁን ላይ ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ እየሆኑ እንደሆነም ነው ያስረዱት።
ምሁራኑ እንዳነሱት ከግለሰቦች ባለፈ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አክቲቪስቶችም ለጉዳዩ መባባስ ተሳታፊዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
አንዳንድ ግለሰቦች ለለውጡ መልካም ነገር ያበረከቱ ቢሆኑም እንቅስቃሴያቸውና በማህበራዊ ሚዲያ የከፈቱት ዘመቻ ትክክል ባለመሆኑ ለህግ መገዛት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የጥላቻ ንግግርን በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩ አካላት የሚያስተላልፉበትን ቋንቋ ሌላው አያውቀውም ብለው ማሰብ ተገቢ እንዳልሆነም አውስተዋል።
የየራሳቸው ክበብ ሰርተው በጥላቻ ንግግር ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጥፋት እየተጉ ያሉ አንዳንድ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህ ከፖለቲከኛና የአገርን ጥቅም አስጠብቃለሁ ከሚል የማይጠበቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዶክተር ጠና ደዎ እንዳሉት ከአክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ነን ከሚሉ የጥላቻ ንግግር የሚደመጥ ከሆነ እነዚህ እውነተኛ እክቲቪስቶች አይደሉም፤ ኃላፊነት የማይሰማው ፖለቲከኛ ደግሞ ፖለቲከኛ ሊባል አይችልም ብለዋል፡፡
የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል ማህበራዊ ሚዲያን መዝጋት መፍትሄ ባይሆንም መንግስት በኃላፊነት መጠቀም የሚያስችል ህጋዊ ማዕቀፍ በአፋጣኝ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ዶክተር ጠና መክረዋል።
የፖለቲካ ድርጅቶችም በመሰል ተግባር ላይ የሚሳተፉ አክቲቪስቶቻቸውን አቅጣጫ በመስጠት ማረም አለባቸው ብለዋል።
ህብረተሰቡን ከማስተማር ባለፈ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮችን ተከታትሎ ትንተና መስጠትና እውነታውን የማሳወቅ ስራ ከመገናኛ ብዙሃን እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
ወደ ቀድሞው ላለመመለስና ለውጡን ለማስቀጠልም መንግስትና ፖለቲከኞች ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ልሂቃን የተባሉ አካላትም የጉዳዩ ተሳታፊዎች መሆናቸውን የገለፁት ምሁራኑ በመማር አገርን ከውድቀት የመከላከል ሚናን መወጣት ካልተቻለ አዋቂ መባል ትርጉም አልባ ይሆናል ነው ያሉት።
ህብረተሰቡ በበኩሉ ሰላሙንና አብሮ የመኖር እሴቶቹን ለመጠበቅ በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር ለሚያስተላልፉ አካላት ምላሽ ከመስጠት መቆጠብ እንዳለበት አሳስበዋል።
አቶ ግደይ ደገፉ እንደሚሉት መጥፎ ለፃፈ መልስ መስጠት አያስፈልግም ፤ጥሩ ለፃፈ ደግሞ እዛ ላይ መከራከርና መስተጋብር መፍጠር ያስፈልጋል ፤ አለዚያ መጥፎ ለፃፈው መጥፎ መፃፍ የሚፈልገውን አገኘ ተስፋፋ ማለት ነው ብለዋል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ የሚነገሩ የጥላቻና የሃሰት ወሬዎች በአገር ገፅታ ላይ ተፅእኖ እንዳላቸው የቅርብ ጊዜው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ማሳያ ነው።
በአደጋው ወቅት ኢትዮጵያዊያን ጭምር ያልተገባና ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ማስተላለፋቸውን የአቢሲኒያ በረራ አገልግሎት ባለቤት ካፒቴን ሰለሞን ግዛው እንዲህ ገልፀውት ነበር።
"የውሸት መረጃዎችን፣ የውሸት አሉባልታ ወሬዎችን፣ አላስፈላጊ ይህን ፖለቲካዊ ለማድረግ ይህን ሌላ ነገር ለማድረግ የፈጠራ ታሪክ እያወሩ፣ ያልሞቱ የአየር መንገዱ የስራ ባልደረቦች ፎቶ እየለጠፉ ነፍስ ይማር ማለት ከዚህ የበለጠ ሽብር ያለ አይመስለኝም እና በዚህ በፌስ ቡክ በተለያዩ ሚዲያዎች የምንጠቀማቸው ነገሮች ኃላፊነት ቢኖርበት የአገር ፍቅር ትንሽ ቢታይበት በቃ እግዚአብሄርን መፍራት የሚታይበት ቢሆን ደስ ይለኛል።" ብለዋል፡፡