ቀጥታ፡

በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ለደረሰው የእሳት ቃጠሎ መንስኤ ሰዎች ናቸው ተባለ

አዲስ አበባ  መጋቢት 27/2011በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ  ሆን ተብሎ በሰዎች የተፈጸመ ነው ሲል የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለፀ።

በኢትዮጵያ ጥበቃ ከሚደረግላቸው 27 ብሔራዊ ፓርኮች መካከል የሆነው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በአማራ ከልል ሰሜን ጎንደር ውስጥ ይገኛል።

በአጠቃላይ 412 ኪሎሜትር ስኩየር ስፋት ያለው ይህ የተፈጥሮ ቅርስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከፍተኛ የእሳት አደጋ ደርሶበታል።

በቃጠሎውም 340 ሔክታር የሚሆነው የፓርኩ ደን ጉዳት እንደደረሰበት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቋል።

በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት ቦታዎች ልማትና ጥበቃ ዳሬክተር አቶ ግርማ ቲመር ለኢዜአ እንደተናገሩት ላለፉት 10 አመታት ፓረኩን ከሰው ንክኪ መጠበቅ ተችሎ የነበረ ቢሆንም ሰሞኑን ግን ሰዎች ሆን ብለው በለኮሱት እሳት ቃጠሎው ተከስቷል።  

"የእሳት አደጋው 'ጨነቅ' በተባለ አካባቢ ከተከሰተ ከአራት ሰዓታት በኋላ ሳንቃ በር ወደሚሰኝ አካባቢ ተዛምቷል፤ ቃጠሎ ሲነሳም በፓርኩ ውስጥ ሰዎች እንደታዩ ከአይን እማኞች ማረጋገጥ ተችሏል" ብለዋል። 

ተጠርጣሪዎችን ለመለየት ጉዳዩ በፖሊሲ ምርመራ ላይ እንደሚገኝም ዳሬክተሩ አስረድተዋል።

እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ በፓርኩ የሚገኘው "ሔሪካ" የተሰኘ የሳር ዝርያ እንደ ነዳጅ የተቀጣጣይነት ባህሪ ስላለው እሳቱን ለመከላከል በተደረገው ጥረት የአንድ ሰው ህይወት ጠፍቷል።

የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ወጣቶችና የጎንደር ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ሶሰት ቀናት በወሰደው እሳቱን የማጥፋት ተግባር ተሳትፈዋል።

የፓርኩ አጠቃላይ ስፋት 412 ኪሎሜትር ስኩየር ሲሆን በቃጠሎው 340 ሔክታር መሬት ተጎድቷል፤ በአሁኑ ወቅት እሳቱ ሙሉ ለሙሉ  ቢጠፋም የመዳፈን ባህሪ ስላለው ድንገት እንዳይነሳ የአካባው ማህበረሰብ እየተከታተለ መሆኑንም አቶ ግርማ ተናግረዋል።

የኢተዮጵያ ሰሜን ተራሮች ፓርክ ዋሊያ አይቤክስ፣ የሰሜን ቀይ ቀበሮ እና ሌሎች ግዙፍ አጥቢ እንስሳትን ጨምሮ በርካታ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና ብዝሃ ህይወት መኖሪያ ነው።

ይኸው በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ተደርጎ የተመዘገበው ፓርኩ የብዝኃ-ሕይወት ጥበቃን ለማጠናከር ከማገዝ ባሻገር፤ በአካባቢው ካሉት ዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከልም ነው።

እንደ የዱር እንስሳት ቦታዎች ልማትና ጥበቃ ዳሬክተር አቶ ግርማ ቲመር ገለጻ በዚህ አመት የከፋ የእሳት አደጋ የደረሰባቸው የባሌና ሰሜን ብሔራዊ ፓርኮች ሲሆኑ የሁለቱም መንስኤ ሰዎች ናቸው።

በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በቅርቡ  በተከሰተው ቃጠሎ 2 ሺህ 700 ሄክታር ደን የተጎዳ ሲሆን እሳቱ በሰው ሃይል የጠፋ በመሆኑ አንዳንድ ቦታ ላይ ተዳፍኖ በመቆየት ድንገት ስለሚነሳ በዚህም ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም