የኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነት ወደ ላቀ የቢዝነስ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማደግ አለበት- አምባሳደር መለስ ዓለም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነት ወደ ላቀ የቢዝነስ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማደግ አለበት- አምባሳደር መለስ ዓለም
መጋቢት 26/2011 የኢትዮጵያ እና የኬንያ የሕዝብ-ለሕዝብ ግንኙነት ወደ ላቀ የቢዝነስ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማደግ አለበት ተባለ፡፡
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በኬንያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመገኘት ከአፍሪካ አሕጉር ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፒዩሪቲ ሙሁንዲ ጋር ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለረዥም ጊዜ ሳይቆራረጥ የመጣ መልካም የሁለትዮሽ ወዳጅነት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደር መለስ፤ ግንኙነቱ ለሁለቱ ሀገሮች ሕዝቦች ብልፅግና የላቀ አስተዋፅዎ እንዲያበረክት የኢትዮጵያ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ያለውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የላሙ ፕሮጄክት ትግበራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ አስረድተዋል።
በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ አሕጉር ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሙሁንዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የኬንያ የምንጊዜም ወዳጅ አገር እንደሆነች በመግለጽ በተለይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለተፈረመው የልዩ ደረጃ ስምምነት ትግበራ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው አስታውሰዋል።
በውይይቱ ወቅት ሁለቱ አምባሳደሮች፣ 36ኛውን የኢትዮጵያ-ኬንያ የጋራ የሚኒስትሮች ስብሰባ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡
በቅርቡም የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ያደረጉት ኦፊሴላዊ ጉብኝት ላይ የተደረሱ ስምምነቶች ትግበራን ለመከታተልና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተመሳሳይ ጉብኝት በሚያደርጉበት አግባብ ላይ የበኩላቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ስምምነት ላይ ደርሰዋል ነው ያሉት።
በኬንያ የሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ፣ ማላዊን፣ ሲሸልስን እና ኮሞሮስን እንደሚሸፍን ይታወቃል።