ቀጥታ፡

ኢህአዴግ የጀመረው የመለወጥ ሂደት በአገሪቱ የነበረውን የፖለቲካ መልክ መቀየር ችሏል

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2011 ከመጋቢት 2010 ዓም አንስቶ በድርጅቱ ውስጥ የተጀመረው የመለወጥ ሂደት በአገሪቱ የነበረውን የፖለቲካ መልክ መቀየር እንደቻለ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ገለጸ፡፡

በኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አይዲዮሎጂ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተፈራ ደርበው ስለ ዓመቱ የለውጥ ጉዞ ሲያብራሩ "በአገሪቱ ከዛሬ ዓመት በፊት የነበረው ሁኔታ አስፈሪና አገሪቱንም ከመፍረስ ቋፍ ላይ ያደረሰ ነበር" ብለዋል፡፡

በወቅቱ በኢህአዴግ ውስጥ በነበረው ችግር ምክንያት ህዝቡ ለለውጥ ሲገፋ እንደነበርና በድርጅቱም ውስጥ የመለወጥ ትግል መጀመሩን ነው ኃላፈው የሚናገሩት፡፡

በድርጅቱ ውስጥ የነበረ ጸረ-ዴሞክራሲያዊነት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ፤የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ከዴሞክራሲ ምህዳር መጥበብ፤ ከፍትሃዊ ተጠቃሚነትና እኩልነት መጥፋት ጋር በተያያዘ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን መመለስ ተስኖት ነበር፡፡

በዚህም ሳቢያ ከውስጥም ከውጭም አገሪቱ የመፍረስ አደጋ እንደተደቀነባት ሲተነበይ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ከህዝቡ በመጣው ግፊት አገሪቱን ከገባችበት አደጋ መታደግ የሚችል ትግል በድርጅቱ ውስጥ መካሄድ መጀመሩንና ጠንካራ ውሳኔ መወሰኑን የጠቀሱት አቶ ተፈራ ውሳኔውንም "ከሞላ ጎደል ለአብዮት የተቃረበ የሪፎረም ውሳኔ" ሲሉ ገልፀውታል፡፡

በአገሪቱም ሆነ በድርጅቱ ውስጥ የፖለቲካ ማሻሻያ ታውጆ ይህንንም መምራት የሚችል የአመራር ለውጥ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪ በድርጅቱ ውስጥ የተሟላ የአሰራር ቁመና ለመያዝ የሚያስችል ማሻሻያ እንዲደረግ፣ መንግሰት የአሰራርና አመራር ለውጥ እንዲደረግ፤ ለጸረ-ዴሞክራሲ አካሄድ ሲረዱ የነበሩ ህጎች እንዲሻሻሉና እንዲቀየሩ፣ በኢኮኖሚ ዘርፍ ማሻሻያ እንዲደረግ መወሰኑ አንኳር እርምጃዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ከአገር ውጭ የነበሩ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ወደ አገር መመለሳቸው፣ ውይይትና ድርድር መጀመሩ፣ ሚዲያና ዜጎች በነጻነት መንቀሳቀስ መጀመራቸው፣ በደህንነት ተቋሙና በፀጥታ መዋቅር የተሰሩ ስራዎች፣ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ የተወሰዱ እርምጃዎች፣ በዲፕሎማሲ መስክ የተገኙ ድሎች፣ እርቅ፤ ሰላምና መቀራረብ እንዲወርድ መደረጉም የለውጡ አንኳር ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡

በኢህአዴግ ውስጥ በለውጡ ምንነትና አቅጣጫ ላይ የተሟላ መግባባትና የሃሳብም ሆነ የተግባር አንድነት አለመኖሩን ደግሞ እንደ ቀዳሚ ተግዳሮት ጠቅሰዋል፡፡

የህግ የበላይነትና ሰላምን ማረጋገጥ ፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ቀጣይነት ያለው የውጭ ምንዛሪ ግኝት፤ በብሄራዊ ማንነትና ኢትዮጵያዊነት መካከል ያለው ትስስር፣ በሃሳብና በውይይት ብቻ ልዩነቶችን መፍታት ላይ የሚታዩትን ክፍተቶችንም እንዲሁ በተግዳሮትነት አንስተዋል፡፡

ለውጡን ለማስቀጠል ድርጅቱ በእነዚህ ችግሮች ዙሪያ ከህዝቡና ከተለያዩ አካላት ጋር ጠንካራ ስራዎችን እንደሚሰራ አቶ ተፈራ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም