ቀጥታ፡

የአየር ብክለት የሚያስከትሉ ኢንዱስትሪዎችን መቅጣቱ ይቀጥላል--የኦሮሚያ ክልል

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2011 በኢንዱስትሪዎች የሚፈጠር የአየር ብክለትን በመቀነስ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡትን ማበረታታትና ችግር ያለባቸውን መቅጣቱን እንደሚቀጥል የኦሮሚያ ክልል አስታወቀ።

የደንና አየር ንብረት ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ ሁለት የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ፣ ቀደም ሲል እርምጃ ተወሰዱ ያስተካከለና ሁለት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው በማስተካከል ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የግብርና ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የስራ ኃላፊዎቹ ከባለሃብቶች ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን ለአየር ንብረት ስጋት በሆኑት ላይ እርምጃ መውሰድና ያስተካከሉትን ደግሞ እውቅና የመስጠት ስራ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

ተረፈ ምርት ማከሚያ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅና አንዳንድ ፋብሪካዎች ማከሚያ ሳይኖር ተረፈ ምርታቸውን እየለቀቁና እያመረቱ በገበያ ተወዳዳሪነታችን ላይ ችግር እየፈጠሩብን ነው ሲሉ ባለሃብቶች አመልክተዋል።

ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ በበኩላቸው መንግስት ይህን እንደማይታገስና የአየር ንብረት ብክለት የሚያስከትሉ ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

መንግስት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ማስተካከያ ያደረጉና ጥሩ አፈጻጸም ያላቸውን እንደሚያበረታታም አክለዋል።

የአየር ንብረት ብክለት ተጽዕኖን በመቀነስ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ፋብሪካዎች ነገ አዳማ ላይ እውቅና እንደሚሰጣቸው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም