ወደ ውጭ ከተላኩ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ከ9 ሚሊዮን በላይ የውጭ ምንዛሬ ተገኘ

11

መቀሌ መጋቢት 26/2011 በመቀሌ ከተማ አካባቢ ከሚገኙ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ውጭ ከተላኩ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን  ዩሮ እና 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን በኢትዮጵያ ጉምርክ ኮሚሽን የመቀሌ ቅርንጫፍ አስታወቀ።

በቅርንጫፉ የትምህርትና ድጋፍ ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ታዴዎስ ተስፋ  እንደገለጹት የውጭ ምንዛሬው የተገኘው  ቮሎሲቲ፣ ዲቢኤልና ኢታካ የተባሉ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች እና ወደኢንዱስትሩ ፓርኩ በገቡ ባለሀብቶች ተመርተው ወደ ውጭ ከተላኩ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች ነው።

በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከገቡት ስድስት የውጭ ባለሀብቶች መካከል ሁለቱ ባለሀብቶች ምርታቸውን ወደ ውጭ መላክ መጀመራቸው ታውቋል፡፡

አስተባባሪው እንዳሉት ባለፉት ስምንት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል።

ከእዚህ በተጨማሪ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰው፣ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶቹ ወደ አውሮፓና አሜሪካ የተላኩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለጻ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የተሻለ እንዲሆን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ለባለሀብቶች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

የመቀሌ  ኢንዱስትሪ ፓርክ  አገልግሎትን  ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግም በሥራ ሂደት የሚመራ የሥራ ክፍል ተመድቦ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አቶ ታዴዎስ አመልክተዋል፡፡

በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎይተኦም ገብረኪዳን በበኩላቸው በፓርኩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ የተሰሩት 15 ሼዶች በስድስት ባለሀብቶች መያዛቸውን አስረድተዋል።

ወደ ሥራ የገቡ ባለሀብቶች ለሁለት ሺህ  ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ አንድ ኩባንያ የፊታችን ሚያዚያ ወር ምርቱን ወደ ውጭ ለመላክ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኩ የተገነቡ ሁሉም ሼዶች በሁለት ሽፍት ስራ ሲጀምሩ 20 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ መላክ ከጀመሩ ባለሀብቶች መካከል በባንግላዲሽ ባለሀብቶች የተቋቋመው የዱላል ብራዘርስ ሊሚትድ ካምፓኒ  ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አንዱ ነው፡፡

የፋብሪካው ማርኬቲንግ ማናጀር ሚስተር ኑር መሐመድ ሸሙዝ እንደገለጹት በየወሩ እስከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ አልባሳትን ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ወደ አሜሪካና አውሮፓ እየላኩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት መጨረሻ የፋብሪካውን የማምረት አቅም በማሳደግ በየወሩ እስከ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለመላክ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ከአምስት ዓመት በኋላ በየወሩ እስከ 12 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ አልባሳትን አምርቶ ለመላክ መታቀዱን የገለጹት ኃላፊው  አሁን ያሉትን  2 ሺህ ሠራተኞችም እስከ 35 ሺህ የማድረስ እቅድ እንዳለም ጠቁመዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ በሚገኘው በእዚህ  የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ  የሥራ ዕድል ካገኙ ወጣቶች መካከል ወጣት አምለሰት ካህሳይ አንዷ ናት፡፡

ከእዚህ ቀደም በአረብ አገራት በስደት ትኖር እንደነበር ያስታወሰችው ወጣት አመልሰት በአሁኑ ሰዓት  በአቅራቢያዋ በተከፈተው ፋብሪካ የ3 ሺህ ብር ደመወዝተኛ መሆኗን ተናግራለች።

ከጨርቃጨርቅና አልባሳት በተጨማሪ ባለፉት ስምንት ወራት  ወደ ውጭ ከተላኩ የሰሊጥ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቆዳ ውጤቶች፣ ጥራጥሬ፣ የተፈጥሮ ማርና ባህላዊ አልባሳት ከ70 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ መገኘቱን ከኢትዮጵያ ጉምርክ ኮሚሽን መቀሌ ቅርንጫፍ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም