ቀጥታ፡

በይርጋ ጨፌ ከተማ በእሳት አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ

ዲላ መጋቢት 26/2011 በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ይርጋ ጨፌ ከተማ የደረሰ የእሳት ቃጠሎ በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የከተማው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ኢንሰፔክተር ከበደ ገመዴ ለኢዜአ እንደገለጹት በይርጋጨፌ ከተማ ትላንት ማምሻውን በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አንድ ቤት ከሙሉ ንብረቱ ጋር ሊወድም ችሏል።

በከተማው በተለምዶ ደንቦስኮ ሰፈር በሚባለው አከባቢ በ25 ሊትር ጀርካኖች ተቀድቶ የተቀመጠ ነዳጅ ፈንድቶ እሳት ማንሳቱን ተከትሎ አደጋው መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡

በአደጋው የስድስት ወር አራስ እናትና ልጇን ጨምሮ የሶስት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ አንድ ሰው ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶበት በይርጋጨፌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የህክምና ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን ተናግረዋል።

"ቃጠሎው ወደ ሌሎች ቤቶች እንዳይዛመት ወጣቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር ባደረጉት ጥረት ለማስቆም ተችሏል" ያሉት ኢንስፔክተሩ አደጋው በደረሰበት ቤት የችርቻሮ የነዳጅ ሽያጭ ይካሄድ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በከተማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጎዳና ላይ የነዳጅ ሽያጭ መበራከቱን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ንረትና እጥረት ከመታየቱም ባለፈ ለተለያዩ አደጋዎች መንስኤ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት ከሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ባለፈ በአያያዝና አጠቃቀም ጉድለት ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም