ቀጥታ፡

ሃገር በቀል ባህልና እውቀት ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል...ምሁራን

ደሴ መጋቢት 26/2011 ሃገር በቀል እውቀትና ባህል ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቶት እንዲዳብር አለመደረጉ ላለመግባባትና ለሰላም መታጣት የራሱ ድርሻ እንዳለው ምሁራን ገለጹ።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ ሲካሄድ የነበረው ሶስተኛዉ ሀገር አቀፍ የቋንቋና ባህል አውደ ጥናት በቀረቡ 24 ጥናቶች ላይ በመወያየትና የማዳበሪያ አስተያየት በመስጠት ተጠናቋል።

በዩኒቨርሲቲው የቋንቋ ትምህርት ቤት መምህር ዶክተር እንድሪስ ዓባይ "የባህል ብልሃቶችን መማርና አንብቦ መረዳት" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳመለከቱት የኢትዮጵያ የጥንት ባህሎችና ቋንቋዎች በውጪው ባህል ተበርዘው ይዘታቸውን እያጡ ነው።

የግጭት አፈታት፤ሽምግልና፤መከባበርና የመቻቻል ባህሎች ከመረሳታቸውም ባለፈ በራስ ቋንቋ ሀገር በቀል እውቀትን መግለጽ አለመቻል ማህበረሰባዊ ችግር እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

ትውልዱ ሀገር በቀል እውቀቶችንና ጥንታዊ ጹህፎችን የሚረዳበት የመረጃ ማዕከልና ክምችት ማዘጋጀት፤አባቶችና ሽማግሌዎች በየእምነት ተቋማቸው ታሪክና ባህልን ማስተማር መፍትሄዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ወሎ ዩኒቨርሲቲ የግዕዝና አረብኛ ቋንቋዎችን ማስተማር መጀመሩ በዚህ ረገድ የራሱን አወንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

"ነገረ ጊዜ፤በዝጎራ ረጅም ልቦለድ" የሚል ጥናታዊ ጽህፍ ያቀረቡት የጅማ ዩንቨርሲቲ የፎክሎርና ጽነ-ጹህፍ መምህር ዶክተር ለማ ንጋቱ በበኩላቸው እንዳመለከቱት ባህሎቻችንን ለሌሎች ለማስተላለፍ ጠንቅቆ ማወቅ ይቀድማል፡፡

ከአባቶች ጠጋ ብሎ ከመጠየቅና ከመረዳት ይልቅ ማጥላላትና መናናቅ፤ለየሐይማኖቱ ታማኝ አለመሆን፤ለጊዜያዊ ጥቅም መታለልና ለስሜት መገዛት ልዩነትና አለመግባባትን መፍጠሩን አስረድተዋል።

በተለይ ወላጅና ጎረቤት ልጆችን በጥሩ ስነ-ምግባር ተንከባክቦ ከማሳደግ ይልቅ የጦርነት ፤ የድብድብ፤ የብልግና እና የተንኮል ፊልሞችን እንዲያዩ መፍቀዱ ባህላቸውን እንዲረሱና ማህበራዊ ህይወት እንዳይለምዱ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም መንገድ የሚዘጋ፣ ታላቁን የማያከብር የሚዘልፍ፣ ያለምክንያት በመጮህ ሰፈር የሚያውክ ፣ሱሰኛ ትውልድ እየፈጠረ ሰላም፣ አንድነት፣ፍቅርና ተካፍሎ መብላት እንዳይኖር እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል።

ማስተማር፣ መገሰጽ፣ ለልጅ የማይመጥኑ የፊልምና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞችን እንዳይጠቀሙ መከልከል፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ ከፋፍለው እንዲጠቀሙ ማድረግ ዋነኛው መፍትሄ መሆኑንም አስቀምጠዋል፡፡

በሽማግሌዎች መዳኘት፣በአባቶች መመራት ለዘላቂ ሰላም እገዛ እንዳለው የገለጹት ደግሞ "ባህላዊ ግጭት አፈታትና ተግዳሮቶቹ" በሚል ርዕስ ጥናት ያቀረቡት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ልማት ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ይመር አሊ ናቸው፡፡

ባህልን ሳያዛባ ለተረዳው ሰላምና አንድነት ከመፍጠሩም ባለፈ ፖለቲካዊ፤ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግልጋሎቱም ከፍ ያለ እንደሆነ አስረድተዋል።

"በሀገር በቀል እውቀትና በባህላዊ ሽምግልና አለመግባባቶችን መፍታት ወጭን፣ ጊዜን፣ መደበኛ ስራን ከማቃለሉም በተጨማሪ ቂም በቀል የሌለበት ዘላቂ ሰላምና ይቅር ባይነትን ይፈጥራል"ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል እሴቶች ልማት ባለሙያ አቶ አዝመራው በየነ በበኩላቸው "የቀረቡ ጥናቶች ማስተካከያ ተደርጎላቸው ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ቢሮው ይሰራል" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክ፣ ወግና ቋንቋ ሳይዛባ ለማስተማር ከሐይማኖት አባቶችና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር በቁርኝት መስራት መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ የሁለት ቀን ቆይታ ከ15 ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የቀረቡ ጥናቶችን ገምግመው የማስተካከያ ሃሳብ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም