ቀጥታ፡

የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ የቅድመ ምርመራ ውጤት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ የቅድመ ምርመራ ውጤት ይፋ ሆነ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ አደጋውን ለመመርመር ከተዋቀረው ቡድን ጋር በመሆን የአውሮፕላኑን አደጋ አስመልክቶ የተካሄደውን የቅድመ ምርመራ ውጤት ገልጸዋል።

አውሮፕላኑ ለጉዞ ከመንቀሳቀሱ በፊት ሙሉ የመብረር አቅም ያለውና በትክክለኛው መስመር መብረር በሚያስችለው ሁኔታ ላይ እንደነበረ ተናግረዋል።

የአብራሪዎቹ ብቃት የተሟላና አውሮፕላኑም ሙሉ ለሙሉ የመብረር አቅም እንዳለው የሚያሳይ ሰርተፍኬት እንዳለውም በምርመራው ተረጋግጧል።

በአደጋው ጊዜ አብራሪዎቹ የአውሮፕላኑ አምራች ኩባንያው አደጋ መቆጣጠር ያስችላል ያለውን ቅደም ተከተል በመፈጸም አደጋውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት አለመሳካቱን ምርመራው እንዳመላከተ ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

የመጀመሪያውን ዙር የምርመራ ውጤት ተከትሎ በቀጣይ ትኩረት ይሻሉ በተባሉ ምክረ ሃሳቦች አምራች ኩባንያው የአደጋ መቆጣጠሪያ ስርዓቱን ሊያሻሽልና ሊፈትሽ እንደሚገባ ተገልጿል።

የአውሮፕላኑ ስሪት ወደ በረራ ከመመለሱ በፊት በዘርፉ የሚሳተፉ አካላት በበረራ ወቅት የሚያጋጥምን የመቆጣጠር ችግር የሚያስወግድ የቁጥጥር ስረዓት ማረጋገጥ ይገባቸዋልም ብለዋል ሚኒስትሯ።

የቦይንግ ኩባንያ የሶፍትዌር ማሻሻያ ማድረጉን፣ በምርመራው ላይ የነበረው ተሳትፎና ቀሪ መረጃዎችን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ሚኒስትሯ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአውሮፕላን አደጋ ላይ የሚካሄድን ምርመራ አደጋው የደረሰበት አገር በባለቤትነት የሚመራው ቢሆንም አምራች ኩባንያውና አገሩ፣ ዲዛይነርና የአውሮፕላኑ ከፍተኛ ሙያተኞች የተካተቱበት ቡድን ምርመራውን የማካሄድ ግዴታ እንዳለበት ዓለም አቀፉ ህግ ይደነግጋል።

ቅድመ ምርመራው በዚሁ መሰረት እየተካሄደ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

በህጉ የመጀመሪያው ዙር የምርመራ ውጤት በአንድ ወር ውስጥ ይፋ መሆን እንዳለበትና ሌሎች መረጃዎችም በአንድ ዓመት መጠናቀቅ እንዳለባቸው የተቀመጠ በመሆኑ በዚሁ መሰረት የሚካሄድ ይሆናል ብለዋል።

የምርመራውቡድን መሪ አቶ አምዴ አያሌው በበኩላቸው አደጋው በደረሰበት ወቅት አውሮፕላኑ ላይ ምንም አይነት ውጫዊ አደጋ እንዳልደረሰበት በምርመራው መረጋገጡን ገልጸዋል።

በአደጋው ወቅት አውሮፕላኑ ከውጭ ተመቷል፣ አደጋ ደርሶበታል የሚል የሀሰት መረጃ መናፈሱን አስታውሰው ምርመራው ምንም አይነት ውጫዊ ጉዳት እንዳልደረሰበት አረጋግጧል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ኬንያ መጓዝ በጀመረ በስድስት ደቂቃ ውስጥ በመከስከሱ 157 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ የሚታወስ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም