የብዙሀን መገናኛ በመርህ ላይ የተመሰረተ የፍርድ ቤት ነክ መረጃዎችን ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የብዙሀን መገናኛ በመርህ ላይ የተመሰረተ የፍርድ ቤት ነክ መረጃዎችን ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተጠቆመ
አዳማ መጋቢት 26/2011 የብዙሀን መገናኛ በመርህ ላይ የተመሰረተ የፍርድ ቤት ነክ መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራምና ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር " በፍርድ ቤቶች ውሎ አዘጋገብና የስነምግባር መርሆዎች ላይ " ለብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ የብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎችና ዘጋቢዎች የፍርድ ቤት ነክ መረጃዎችን ሲዘግቡ ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ጥንቃቄ ሳያደርጉ ለህዝብ የሚለቁት መረጃ የፍርድ ቤትን ነፃነትና ገለልተኝነት ሚዛን የሚያዛባ የሚሆንበት አጋጣሚ እየተበራከተ መምጣቱንም ተናግረዋል።
አቶ ሰለሞን እንዳሉት ጥንቃቄ ሳይደረግበት የሚለቀቅ መረጃ ሕብረተሰቡ አሉታዊ ግንዛቤ በመያዝ በፍርድ ቤቶች ላይ የሚኖረውን እምነት ይሸረሽራል፤ ፍርድ ቤቶችም የተበላሸ ገፅታ እንዲኖራቸው ያደርጋል።
በተለይየፍርድ ቤት ጉዳዮችን በተመለከተ ከብዙሀን መገናኛ የሚሰራጨው መረጃ ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ፣ እውነት ላይ ያልተመሰረተ፣ የሚሰራጨው መረጃ የሚያስከትለው ውጤት አስቀድሞ ግምት ውስጥ ካልገባና በዘፈቀደ የሚመራ ከሆነ ሕብረተሰቡ አሉታዊ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ያደርጋል” ብለዋል።
ችግሩን ለማቃለል በመርህ ላይ የተመሰረተየፍርድ ቤት ነክ ዘገባዎችን መስራት የሚያስችል የኮሚዩኒኬሽን ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመቀየስ ጀምሮ የሚዲያ ባለሙያዎችን የማሰልጠን ተግባር መጀመሩን አስታውቀዋል።
እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ መድረኩም የእዚህ እንቅስቃሴ አካል ነው።
"መድረኩ ለሚፈጠር ግጭት ህግን ብቻ መሠረት አድርጎ ፍትሀዊ ዳኝነት እየተሰጠ ስለመሆኑ ከማስገንዘብ ባለፈ ሚዲያው ገለልተኛ ሆኖ ተዓማኒነት ያለው መረጃ ለሕብረተሰቡ በነጻነት ተደራሽ እንዲያደርግ ያለመ ነው" ብለዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ዋስትና የሚሰጥ ፍርድ ቤት ስለመኖሩ ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥ የብዙሀን መገናኛ ባለሙያ ለማፍራት ጭምር መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተስፋዬ በበኩላቸው "የፍትህ መስፈን ለሁሉም ዘርፍ ወሳኝ በመሆኑ የብዙሀን መገናኛዎች በእውቅት ላይ የተመሰረተና ጥልቀት ያለው ዘገባ ሊዘግቡ ይገባል" ብለዋል።
በፍትህ ጉዳይ ላይ መንግስትን የሚተችና ትምህርት ሊሰጥ የሚችል መፍትሄ አዘል ዘገባ በማከናወን ለሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይ በፍርድ ቤት ውሎ አዘጋገብ ላይ ሁሉም ብዙሀን መገናኛዎች ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ስልጠናው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በፍርድ ቤት ነክ ጉዳዮች አዘጋገብና መረጃ አሰጣጥ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋትና ክህሎታቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የስልጠና መድረክ ላይ ከመንግስትና ከግል የብዙሀን መገናኛ ተቋማት የተውጣጡ የሕትመትና ብሮድካስት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።