ቀጥታ፡

ለውጡ የኦሮሚያ ፖሊስን እንድንቀላቀል አድርጎናል--- የቀድሞ የኦነግ አባላት

አዳማ መጋቢት 26/2011 ለውጡ የፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የኦሮሚያ ፖሊስን ተቀላቅለናል ሲሉ ተመራቂ የቀድሞ የኦነግ አባላት ገለፁ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የሰጣቸውን ስልጠና አጠናቀው ሰሞኑን ከተመረቁ የቀድሞ የኦነግ አባላት መካከል ረዳት ሳጂን ሳሚር ጂሃድ እንደገለፀው ከጅማ ዞን አጋሮ ከተማ ወደ ግንባሩ በመቀላቀል በኤርትራ ሆኖ ለፍትህና ለእኩልነት ሲታገል ቆይቷል።

" የትግላችን ዓላማ ለዴሞክራሲና ለህዝቦች ነፃነት በመሆኑ በህዝቦች የጋራ ትግል በመጣው ለውጥ የሀገሪቷ የፖለቲካ ምህዳር ተቀይሯል" ብሏል ፡፡

የትጥቅ ትግሉን በመተውና ትጥቅ በመፍታት ለሰላማዊ ትግል ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ተናግሯል ።

በራሱ ምርጫ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ በመቀላቀል ስልጠና መውሰዱንም አመልክቷል።

"አባቴ አሁንም በኦነግ ስም በጫካ ሆኖ የትጥቅ ትግል ላይ ይገኛል " ያለው ረዳት ሳጂን ሳሚር፣ የኦሮሞ ህዝብ የፍትህ፣ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ምላሽ እያገኘ በመሆኑ ትጥቅ ያልፈቱ የኦነግ አባላት ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል ።

ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የትጥቅ ትግሉን በመተው ወደ ሰላማዊ ትግል መመለሳቸውን የገለጹት ደግሞ ረዳት ሳጅን አበራ ኦሊ ናቸው።

ለአስር ዓመት የሀገር መከላከያ አባል ሆነው ካገለገሉ በኋላ ጭቆናና ግፍን በመቃወም ግንባሩን ተቀላቅለው በኤርትራ ትግል መጀመራቸውን አስታውሰዋል ።

ላለፉት 14 ዓመታትም ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲና ለእኩልነት መታጋላቸውን የገለጹት ሳጅን አበራ ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን ለመወጣት የኦሮሚያ የፀጥታ ኃይልን መቀላቀላቸውን ገለጸዋል ።

በተለያዩ አካባቢዎች በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ባልደረቦቻቸው ለውጡ የፈጠረውን  ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለሱም ረዳት ሳጂን አበራ ጠይቀዋል ።

ረዳት ሳጂን አብዱረሃማን አህመድ በበኩሉ ከኢሉ አባ ቦራ ዞን በደሌ ወረዳ ወደ ትጥቅ ትግሉ እንደተቀላቀሉ ገልጻል።

"በሀገሪቱ ፍትህና እኩልነት እንዲመጣ የታገልንለት ዓላማ ተሳክቶ ለውጥ በመምጣቱ ደስተኛ ነኝ" ብሏል ።

ረዳት ሳጅን አብዱረሃማን እንዳለው ወደ ሰላማዊ ትግል ያልተመለሱ አባላት ትጥቃቸውን ፈተው ሊቀላቀሉ ይገባል ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታቸው ኢታ " የግንባሩ አባላት ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ የተደረገው በሀገሪቷ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ነው " ብለዋል።

ኮሌጁ 697 የግንባሩ የሠራዊት አባላትን ተቀብሎ በማሰልጠን የክልሉን  የፀጥታ ኃይል እንዲቀላቀሉ ማድረጉንም ኮማንደር ጌታቸው አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም