በሀገሪቱ የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር ወጥነት ይጎለዋል - የህግ ምሁር - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር ወጥነት ይጎለዋል - የህግ ምሁር
መጋቢት 26/2011 በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር ወጥነት እንደሚጎለው የህግ መምህሩ አቶ መሃመድ ዳውድ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናገሩ፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ መሃመድ ዳውድ እንደሚሉት በአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ለውጡ እንደተጀመረ ተስፋ ሰጭ ጅማሮዎች ቢታዩም እየቆ በለውጥ ሂደቱ ስር-ዓተ አልበኝነት እየታየ መጥቷል፡፡
ለውጡን ተከትሎ ከተወሰዱ መልካም እርምጃዎች መካከል አለአግባብ የታሰሩ ሰዎች መፈታት፣ችግር የነበረባቸው ህጎችን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች፣በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለግህ ለማቅረብ የተደረጉ ጥረቶችን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ስኬቶች ይኑሩ እንጂ በለውጥ ሂደቱ የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንጻር ክፍተት መኖሩን የሚናገሩት አቶ መሃመድ፤ “ዜጎች በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የመኖር፣ ተንቀሳቅሰው የመስራት ህገመንግስታዊ መብታቸው ተጥሶ በየቦታው ተፈናቅለዋል” ይላሉ፡፡
ችግሩ የተከሰተው መንግስት አቅም ስላነሰው ነው የሚል እምነት እንሌላቸው የገለጹት አቶ መሃመድ፤ “ዜጎችን በእኩል አይን ካለማየት የመነጨ ነው” ይላሉ፡፡
’’መንግስት መታገስ በሚፈልግበት ጉዳይ ይታገሳል፤ በሌላ በኩል በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን የሚጠይቁትን ያንገራግራል፤ ይህም ለውጡ በሚፈለገው ልክ እንዳይቀጥል ያደርጋል’’ ነው ያሉት፡፡
በሙስና፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር እንደ አጀማመሩ አለመቀጠሉ በለውጥ ሂደቱ የህግ ማስከበር ተግባሩ ወጥነት እንደሌለው ያሳያል ያሉት መምህሩ፤ ይህ ስርዓተ አልበኝነት እንዲስፋፋ ያደረጋል ብለዋል፡፡
ለውጡ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ነባር ህጎችንም ሆነ አዳዲስ የተሻሻሉ ህጎችን ለህብረተሰቡ በሚገባ ማስተዋቅ፣ ተግባር ላይ ማዋልና ህጎች እንዳይጣሱ መስራት ያስፈልጋል የሚል ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል።
ማህበራዊ ሚዲያ በህግ ማስከበሩ ተግባር የራሱ አሉታዊ ተጸእኖ ስላለው አስፈላጊው ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በበኩሉ በተለያዩ አካባቢዎች ለዜጎች መፈናቀል፣ ለንብረት መውደምና ተያያዥ ወንጀሎች የተጠረጠሩ አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ ነው ብሏል፡፡
በጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ እንዳሉት በሃገሪቱ አንዳአንድ አካባቢዎች፤ በቤኔሻንጉል፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ አንዳአንድ አካባቢዎች ችግር የፈጠሩ አካላት ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተደረጉ ጥረቶች ማሳያ ናቸው።
ስርዓተ አልበኝነት እንዲሰፍን ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ በየደረጃው በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ለውጡን የማይፈልጉ የአመራሮችም በህግ እንዲጠየቁ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የህግና ፍትህ ሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ለህግ የበላይነት መከበር የራሱ ድርሻ እንዳለው ያብራሩት ዳይሬክተሩ የሚዲና መረጃ ነጻነት አዋጅ፣ የጸረ ሽብር አዋጅና የሲቪል ማህበራት አዋጅ ማሻሻያ እየተደረገባቸው መሆን ገልጸዋል፡፡
ለግጭትና ብጥብጥ የሚዳርጉ ተግባራትን ለመግታትም የጥላቻ ንግግርን ጨምሮ አዳዲስ የህግ ማዕቀፎችም እየተረቀቁ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡