ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት በመቱ ለሚገነባው የምርት ማከማቻ መጋዘን የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት በመቱ ለሚገነባው የምርት ማከማቻ መጋዘን የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
መቱ መጋቢት 26/2011 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ60 ሚሊዮን ብር በመቱ ከተማ ለሚያስገነባው የምርት ማከማቻ መጋዘን የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ ናቸው የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት።
3 ሺህ 200 ካሬ ሜትር ስፋት የሚኖረው 23ኛው የምርት ገበያው መጋዘን ከኢሉባቦርና አካባቢዋ ዞኖች ምርቶችን ለመሰብሰብ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አቶ ወንድምአገኘሁ ተናግረዋል።
በኢሉባቦር ዞን ከ172 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በየአመቱ ከ80 ሺህ ቶን በላይ ቡና እንደሚመረት ምርት ገበያው አስታውቋል።
የዞኑ ማህበረሰብና አስተዳደር ከቅርንጫፍ ይከፈትልን በተጨማሪ በቡና የግዢ ውል ውስጥ የኢሉአባቦራ ቡና የራሱ ስያሜ እንዲሰጠው ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ከዞኑ የሚቀርበው ቡና “የኢሉአባቦራ ቡና” በሚል ስያሜ በአዲሱ ኮንትራት ውስጥ እንዲገለፅና ግብይቱም በዚህ መሰረት እንዲፈጸም መወሰኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡
በስፍራው የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዞኑ ማረሚያ ቤት ታራሚዎች የሰሩትን ፓርክ የጎበኙ ሲሆንከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ እየተወያዩ ነው።