ቀጥታ፡

በቅርቡ የተከሰተው የአውሮፕላን አደጋ ቅድመ ምርመራ ውጤት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ  መጋቢት 26/2011 በቅርቡ በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ላይ የተካሄደው የቅድመ ምርመራ ውጤት ዛሬ ይፋ ሆነ።

የአውሮፕላኑ አምራችንና ዲዛይነሩን እንደዚሁም የኢትዮጵያ መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ አካላት ከአደጋው ማግስት ጀምሮ የአደጋውን መንስኤ የተመለከተ ምርመራ ሲያካሄዱ መቆየታቸውን የትራንሰፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በዚሁ ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት መሰረትም የአውሮፕላኑ አብራሪዎች የበረራ ተግባር ለማከናወን የሚያስችል ፍቃድና የሙያ ብቃት ያላቸው መሆኑ ተረጋግጧል።

በረራው የፀና (ቫሊድ) ሰርተፊኬት ያለው ከመሆኑም በላይ አውሮፕላኑ ለበረራ ሲነሳ በትክከለኛ መስመር መብረር የሚያስችለውና ለመብረርም በተገቢ ቁመና ላይ እንደነበርም መታየቱን ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

አብራሪዎቹ አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ሂደት ቅደም ተከተል መሰረት በማድረግ አደጋውን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረጋቸውም በቅድመ ምርመራ ሪፖርቱ መታየቱን ወይዘሮ ዳግማዊት ገልፀዋል።

የአውሮፕላኑን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተም መርማሪ ኮሚቴው ምክረ ሀሳብ ያቀረበ መሆኑም ተመልክቷል።

በዓለም አቀፍ አሰራረ መሰረትም አጠቃላይ የአደጋውን መንስኤና ሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎችን የሚያብራራው ሪፖርት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

የምርመራው ዓላማ በዓለም አቀፍ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ የበረራ ደህንነት መኖሩን ማረጋገጥ አንጂ ሌሎችን መውቀስ አለመሆኑንም ሚኒሰትሯ አመልከተዋል።

ከአደጋው ማግስት ጀምሮ ዓለም አቀፉ ማሀበረሰብ ላሳየው ትእግስት፣ ድጋፍና ትብብርም ሚኒሰትሯ ምስጋና አቅርበዋል።

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓም በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወቃል።

አደጋውን ተከትሎም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የበርካታ አገራት መንግሰታትና አየር መንገዶች አደጋ የደረሰበትን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከአገልግሎት ውጭ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም