የህዝቡ ጠንካራ ማህበራዊ እሴት ሃገሪቱን በአንድነት አቆይቷታል---ፖለቲከኞች - ኢዜአ አማርኛ
የህዝቡ ጠንካራ ማህበራዊ እሴት ሃገሪቱን በአንድነት አቆይቷታል---ፖለቲከኞች
ባህርዳር መጋቢት 25/2011 የህዝቡ ማህበራዊ እሴት በጠንካራ መሰረት ላይ የታነጸ በመሆኑ ፖለቲካው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ቢደርስም ኢትዮጵያዊ አንድነቱን ጠብቆ ለዛሬ መብቃቱን ፖለቲከኞች ገለጹ።
በሃገሪቱ እየተካሔደ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ክፍተቶች ብቻ ከማጉላት ይልቅ ዘላቂ የመፍትሔ አማራጮችን ማስቀመጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ዛሬ በባህርዳር በተካሔደው ውይይት ላይ "የዴሞክራሲ ባህላችን ያለበት፣ እሴቶቻችንና ልምዶቻችን" በሚል ርዕስ ጽሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በውጣ ውረድ ሲናጥ የኖረ ነው።
የህዝቡ ማህበራዊ እሴቶችና የኢትዮጵያዊ አንድነት አስተሳሰቦች በጠንካራ መሰረት የታነፁ በመሆናቸው ፖለቲካው የከፋ ደረጃ ላይ ቢሆንም ህዝቡ አንድነቱን ጠብቆ እዚህ መድረሱን ተናግረዋል።
"ባለፉት አመታት የህዝቡ ማህበራዊ እሴቶችና አንድነቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ አስተሳሰቦች በፖለቲከኞች ሲሰበክ በመቆየቱ አሁን የህዝቡን ማህበራዊ የጋራ እሴቶችና አገራዊ አንድነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል" ብለዋል።
በመሆኑም ህዝቡ የሀገሪቱ የፖለቲካ አካሄድ እንዳልተመቸው ሲረዳ የመፍትሄው ዋና ተዋናኝ በመሆን ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ ያዳነ ለውጥ ሊያመጣ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
"አሁን እንደ ሀገር ለመጣው ለውጥ ችግሮቹን እንዲያስተካክል ከመንገርና በሚያግባቡ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እየመከሩ መፍትሄ ከማበጀት የተሻለ ሌላ አማራጭ አያዋጣም"ብለዋል።
የለውጥ ሃይሉ አካሄዱን እንዲያስተካክል በማገዝ ለውጡ መላ ኢትዮጵያዊያንን ባግባባ ሁኔታ ዳር እንዲደርስ መደገፍና አገሪቱን አንድ እርምጃ እንድትጓዝ ማድረግ የግድ እንደሚልም ጠቁመዋል።
"የለውጡ ፋይዳዎች፣ቱሩፋቶች፣ፈተናዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች" በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው ለውጡ መነሻና መድረሻው ለመላው ኢትዮጵያዊያን ግልጽ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
"ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ላይ ሲካሄዱ እንደ ነበሩ ለውጦች በጦርነትና በግልበጣ አለመሆኑ ለውጡን ከዜሮ እንዳይጀምር አስችሎታል"ብለዋል።
ያለፈው አንድ ዓመት በርካታ ለውጦች የታዩበት ቢሆንም "የለውጡ አካላት ህግን በማስከበርና ለውጡን ግልጽ ከማድረግ አኳያ መስራት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።
"ኢህአዴግ ስህተቱን አምኖ ለውጡን መቀበሉ ሀገሪቱን ከመበታተን ጫፍ ላይ ታድጓታል" ያሉት አቶ ልደቱ "አሁንም የለውጡ አመራሮች ለውጡን እንዴት እየመሩት እንደሆነና የትስ ሊያደርሱት እንዳሰቡ የለውጡ ግብ ግልጽ አይደለም"ብለዋል።
ለውጡ የዜጎች በነጻነት የመናገር መብት አስከብሮ በውጭ ያሉትንም ለሀገራቸው እንዳበቃ ገልጸው ህገ-መንግስቱ መሻሻል ቢገባውም ሌሎች በርካታ አፋኝ ህጎችን በማስተካከል የዴሞክራሲ ምህዳሩ እየሰፋ በመምጣቱ የጎደለውን መሙላት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
"በብዙ መስዋትነት የመጣን ለውጥ ክፍተቶችን ብቻ አጉልቶ በማሳየት ሳይሆን ክፍተቶችን የማስተካከል ስራ በመስራት ለቀጣይነቱ መረባረብ ይገባል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን ናቸው።
የሃሳብ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እየተቻለ "ትልቁን ጥሎ ትንሹን አንጠልጥሎ መሮጥ ተገቢ አይደልም ለዘላቂ እድገትና አንድነትም አይበጅም” ብለዋል።
"ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት የሚበጅ አሰራርን በጥልቅ ማሰብና ማንበብ ያስፈልጋል አንጂ በነፈሰበት መንፈስ የነጻነት አየር መተንፈስ የጀመረውን ህዝብ ተስፋ ያደበዝዛል"ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬኝን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትና የባህርዳር ከተማ ወጣቶች በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ አንጋፋ የፖለቲካ ሰዎች፣ወጣቶች፣የሃይማኖት አባቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።