ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የዩጋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን አሸነፈ

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የዩጋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን አሸነፈ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እ.ኤ.አ በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ  ዛሬ ባደረገው የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታው የዩጋንዳ አቻውን 3 ለ 2 አሸንፏል።

ጨዋታው ዛሬ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከናውኗል።

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዩጋንዳዊቷ ተጫዋች ናሙኪሳ አይሻ በራሷ መረብ ላይ ስታስቆጥር ሎዛ አበራና ሰርክአዲስ ጉታ ቀሪዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል።

የኢትዮጵያ ቡድን ተደጋጋሚ የጎል እድሎችን መፍጠር ቢችልም በአጨራረስ ድክመት ብዙ እድሎችን አምክኗል።

በተለይ አጥቂዋ ሎዛ አበራ ጎል መሆን የነበረባቸውን አጋጣዎች መጠቀም አልቻለችም።

የዩጋንዳ ቡድን በበኩሉ ግቦቹን ያገኘው ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ነው።

የመጀመሪያውን የዩጋንዳ ጎል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቿ ታሪኳ ዱቢሳ በሯሷ መረብ ላይ ስታሳርፍ ተቀይራ የገባችው ናሱና ሃሲፍ ሁለተኛውን ግብ በስሟ አስመዝግባለች።

ዩጋንዳ ከእረፍት በፊት የፍጹም ቅጣት ምት ብታገኝም ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

የመልስ ጨዋታቸውን ከሦስት ቀናት በኋላ በዩጋንዳ ካምፓላ የሚያደርጉ ሲሆን የኢትዮጰያ ብሔራዊ ቡድን በሚያደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ ድል ከቀናው በቀጣይ ከካሜሮን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚገናኝ ነው የሚሆነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም