"ለአዲስ አበባ የህዝብ ጥያቄዎች ሰላማዊ ትግል እናደርጋለን"- እስክንድር ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
"ለአዲስ አበባ የህዝብ ጥያቄዎች ሰላማዊ ትግል እናደርጋለን"- እስክንድር ነጋ
አዲስ አበባ መጋቢት 25/2011 "ለአዲስ አበባ የህዝብ ጥያቄዎች ሰላማዊ ትግል እናደርጋለን" ሲል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ተናገረ።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳለው፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል።
"የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት" በሚል ራሱን የሚጠራው ምክር ቤትም ማንኛውንም የፖለቲካ ስልጣን የማይፈልግ፣ ለከተማዋ ነዋሪዎች መብትና ተጠቃሚነት ብቻ የሚታገል ነው ሲል ገልጿል።
''የከተማዋ ነዋሪዎችን ጥያቄ ማስመለስ የሚቻለውም በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ብቻ በመሆኑ ከዚህ መሰረታዊ መርህ ውጪ እንቅስቃሴ አናደርግም'' ነው ያለው።
"ይሁንና ከመንግስት በኩል የሚነሳው ውንጀላ የህዝብ ጥያቄዎችን ላለመመለስ ሰበባ ሰበብ የመፈለግ አዝማሚያ ነው የሚል ጥርጣሬ ያሳድራል" ብሏል።
የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በባልደራስ አዳራሽ በተካሄደ ጉባኤ ውክልና እንደሰጡትና የሞራል እና ፖለቲካዊ ውክልና እንዳገኘ ጠቅሶ ''ለህጋዊነት ሂደቱን ጠብቀን እየተጓዝን ነው'' ብሏል።
ባለፈው ቅዳሜ የተከለከለውን ጋዜጣዊ መግለጫ በተመለከተም የፀጥታ ስጋት በመኖሩ ለደህንነት ሲባል መባሉ ተገቢ አለመሆኑንና መንግስት የፀጥታ ስጋት መኖሩን ካወቀ ጥንቃቄ እንድናደርግ ቀድሞ ማሳወቅ እንደነበረበት ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ከሳምንት በፊት የተካሄደው የአዲስ ወግ ውይይት መዝጊያ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር 'የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት' በሚል የሚንቀሳቀሰው ቡድን ህገወጥ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መንግስት ጥሩ ሲሰራ በማመስገን መጥፎ ሲሰራ በመተቸት ከዚህ ውጪ ግን ህጋዊ ባልሆነ አካሄድ የባለ አደራ ምክር ቤት የሚል ድራማ ተቀባይነት እንደሌለው እና በምርጫ የሚፈልጉትን መሪ መምረጥ እንደሚችሉ መጠቆማቸው ይታወቃል።
ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በበኩሉ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ “የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት የነዋሪው ውክልና የለውም” ህጋዊ አይደለም በሚል የሚነሱ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ምንም ዓይነት ህጋዊ መሠረት የሌላቸው እና በስሜት ብቻ የሚንጸባረቁ ናቸው ማለቱ ይታወሳል።
'የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት' በማለት ራሱን የሚጠራው ቡድን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1094/2010 የሚፃረር እና ህገወጥ እንደሆነ በመግለጽም ሁሉም የከተማው ነዋሪ መገንዘብ እንዳለበት መግለጹ ይታወቃል።