የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካን በስምንት ወር ውስጥ ወደ ስራ ለማስገባት ግንባታው ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካን በስምንት ወር ውስጥ ወደ ስራ ለማስገባት ግንባታው ተጀመረ
አዲስ አበባ መጋቢት 25/2011 የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅና በስምንት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ግንባታ መጀመሩን የስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
መንግሥት ለተጀመሩ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ማስፈፀሚያ በቅርቡ ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል መመደቡ ይታወሳል፡፡
ከተመደበው ውስጥ አብላጫው ገንዘብ ላለፉት ስድስት ዓመታት በብረታ ብረትና ኢንጀነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ግንባታቸው ሲካሄድ ቆይቶ ላልተጠናቀቁት የጣና በለስ ቁጥር 1 እና የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካዎች ቀሪ የግንባታ ሥራዎች ማስፈፀሚያ ይውላል፡፡
በአሁ ወቅት በ95 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ቀሪ የግንባታ ሥራው የተጀመረው የጣና በለስ ቁጥር 1 ፋብሪካ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ስኳር ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ቀሪ የግንባታና ተያያዥ ተጨማሪ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ተግባር በዚህ ሳምንት መጀመሩም ተገልጿል፡፡
ግንባታውን ባለፈው እሁድ በይፋ ለማስጀመር የካምስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፈንድቃ ከተማ ነዋሪዎች፣ የአካባቢው ማህበረሰብና የፕሮጀክቱ አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት በሚቀጥሉት ስምንት ወራት ባሉት ጊዜያት ውስጥ የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ ስኳር ወደ ማምረት ይሸጋገራል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ቀሪ ግንባታና አዳዲስ ተያያዥ ሥራዎችን ጨምሮ "ካምስ" ሥራውን ለማካሄድ የተስማማበት 95 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሜቴክ ለዚህ ምዕራፍ ግንባታ ከወሰደው ገንዘብ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑንም ኮርፖሬሽኑ ገልጿል፡፡
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ቀሪ የግንባታ ሥራዎች ለማካሄድ "ጄጄአይሲ" የሚባል የቻይና ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ኩባንያው ያቀረባቸውን ሠነዶች አዋጪ ሆነው ከተገኙ በቅርቡ በኮርፖሬሽኑና በኩባንያው መካከል ውል ተገብቶ ሥራ እንዲጀመር ይደረጋል፡፡
ላለፉት ስድስት ዓመታት በ"ሜቴክ" ግንባታቸው ሲካሄድ የነበረው የጣና በለስ ቁጥር 1 እና የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ አፈፃፀም እንደ ቅደም ተከተላቸው 65 ነጥብ 79 በመቶና 80 በመቶ ላይ እንደደረሰ ኮርፖሬሽኑ በመግለጫው አትቷል።
የሁለቱ ፋብሪካዎች ቀሪ ሥራዎች ተጠናቀው ፋብሪካዎቹ በሙሉ ዓቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ እያንዳንዳቸው በቀን ከ8ሺህ እስከ 10ሺህ ኩንታል ስኳር ያመርታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከስኳር ምርት ጎን ለጎን ኤታኖል የማምረትና የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ከፍተኛ አቅም ይኖራቸዋል፡፡
የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን የሚያካሂደው "ካምስ" የወልቃይት ስኳር ፋብሪካን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ፍላጎቱን የገለፀው "ጄጄአይሲ'' ደግሞ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ስኳር ፋብሪካ ግንባታ የሥራ ተቋራጭ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡