ቀጥታ፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት በጤና መስክ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2011 በአሜሪካ የልማት ተራድኦ (ዩኤስኤይድ) ድጋፍ ባለፉት ሰባት ዓመታት በጤናው ዘርፍ የሰው ሃብት አስተዳደርና የህክምና ባለሙያዎች ሲሰሩ የነበሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በጤና ሰው ሃብት አመራር፣ በአዋላጅ ነርሶች፣ በነርሶች ብቃትና ክህሎት ላይ ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲሰራ የነበረው "ብቁ የሰው ሃብት ለጤና ዘርፍ ፕሮጀክት" ማጠቃለያ መርኃ-ግብር ዛሬ ተከናውኗል።

በዚህ ጊዜ የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን እንደገለጹት፤ በአሜሪካው ዩኤስኤይድ ድጋፍ ላለፉት ሰባት ዓመታት የተተገበረው የጤና ፕሮጀክት ውጤታማ ነበር።

ፕሮጀክቱ በዋናነት በአገሪቷ የነበሩትን የጤና ባለሙያዎች በተለይም አዋላጅ ነርሶችን፣ ነርሶችንና ሀኪሞችን መሰረት በማድረግ በትምህርት ጥራት፣ ጥናትና ምርምር ላይ ከጤና ሚኒስቴር እቅዶችና ከአገሪቷ የጤና ፖሊሲ ጋር በተጣጣመ መልኩ ሲሰራበት ነበር።

በዚህም በሁሉም ክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ከ50 ሺህ በላይ በስራ ላይ የነበሩና አዳዲስ የጤና ባለሙያዎችን አቅም የመገንባት፣ የማሰልጠንና አስመርቆ ወደ ስራ የማስገባት ስራ ተከናውኗል።

ከ20 በላይ ጥልቀትና ስፋት ያላቸው ጥናቶች ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።

በመንግስትና በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በደረጃ የሚሰጡ ስልጠናዎችን ጥራት ከፍ ማድረግ የሚያስችል ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል።

በቀጣይ ከፕሮጀክቱ የተገኙትን ስኬቶች ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለይቶ ለመፍታት ሌላ የ30 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ ዳይሬክተር ዶክተር ዳምጠው ወልደማርያም በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በጤናው መስክ የሰው ሃብት ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራቱ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል።

የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል፣ የምርምርና ጥናት ስራዎች ለፖሊሲ ግብዓት ብቻ ሳይሆን ተጽዕኖ እንዲፈጥሩ ማድረግ ተችሏል።

ስራዎቹ 90 በሚጠጉ የከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የተሰሩ ሲሆን የጤና ተቋማት የሰው ሃብት አስተዳደር ማሻሻል የሚያስችሉ 90 መደቦች እንዲፈጠሩና ስርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶ በሁለተኛ ድግሪ እንዲሰለጥኑ የሚያስችል ስራ ተሰርቷል።

ይህም የጤና ባለሙያና የህዝብ ስብጥር ከነበረበት 1 ነጥብ 3 ወደ 2 ነጥብ 5 እንዲያድግ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከስራ የሚለቁ ስራተኞች ቁጥር ከነበረበት 3 በመቶ ወደ 1 ነጥብ 2 ዝቅ እንዲል ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የዩኤስኤይድ ሚሽን ዳይሬክተር ዶክተር ሌሲሌ ማንሱ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ በጤናው መስክ በአጋርነት ለረዥም አመታት እየሰሩ እንደሆነ ተናግረው ፕሮጀክቱ አጋርነታቸውን የሚያጠናክሩበት ሌላ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ለስኬት እንዲበቃ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ኃላፊነቱን መወጣቱንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም የሚወለዱ ህፃናት ደህንነታቸውና እድገታቸው የተጠበቀ ሆነው ለቤተሰቦቻቸው ደስታን የሚያጎናጽፉ እንዲሆኑ እንዲሁም በጤናው ዘርፍ የሚሰጠው ትምህርት እንዲሻሻል በጋራ እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያና በአሜሪካው ዩኤስኤይድ "ብቁ የሰው ሃብት ለጤና ዘርፍ ፕሮጀክት" እ.አ.አ ከ2012 እስከ 2019 የተተገበረ ፕሮጀክት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም