በታዳጊ ክልሎች ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር አመራሩ ቁርጠኛ መሆን አለበት - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
በታዳጊ ክልሎች ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር አመራሩ ቁርጠኛ መሆን አለበት - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 በታዳጊ ክልሎች ላይ ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር በየደረጃው ያሉ አመራሮች ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ። በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የፌዴራል ልዩ ድጋፍ ቦርድ የ 2010 ዓ.ም የ10 ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለባለድርሻ አካላት አቅርቧል። የኦሮሚያና ደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዞን ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎችን ጨምሮ በሱማሌ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና አፋር ክልሎችን በ2017 ዓ.ም ራሳቸውን ችለው ተቋማዊ አወቃቀር አንዲመሰረት ለማስቻል እቅድ ተይዟል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች የራሳቸውን ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮች ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር። ይሁንና በአመራሮች ቁርጠኛነት ማነስና በአፈፃፀም ድክመት "ድጋፍ የሚሹ ክልሎች አሁን ያሉበት ደረጃ በ 2017ዓ.ም ለመድረስ ከታሰበው እቅድ ወደ ኋላ የቀረ ነው"። ከ 2003 ዓ.ም ጀምሮ በመንደር ማሰባሰብ ስራ ቢጀመርም እንደ ውሃ፣ መብራት፣ መንገድ፣ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋም ያሉ መሰረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው የተሰባሰቡት ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው ሲበተኑ ይታያል። "አካሄዳችን አጥጋቢ አይደለም" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን በሪፖርት ሲቀርቡ የነበሩ የአመራሩ ስራዎች ከኅብረተሰቡ ዘንድ ለውጥ ያላመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። በጋምቤላና በሱማሌ ክልሎች ብቻ ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና ለም መሬት መላ የኢትዮጵያ ህዝብ መመገብ የሚችል ቢሆንም ተቋማዊ አደረጃጀት አለመፈጠሩ የሚገባንን ያህል እንዳንጠቀም አድርጎናል ብለዋል። ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የታዳጊ ክልሎች የራሳቸው ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠርና ያለውን ሃብት መጠቀም እንዳለባት ጠቁመዋል። ይኸንን ግብ ለማሳካትም እስካሁን የመጣንበት አካሄድ "መገታት አለበት" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው አመራሮች መልካም የሚሰሩት እየተመሰገኑ አጥፊዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ በስድስቱ ክልሎች ከሁለት ሚሊዬን በላይ ዜጎችን በመንደር ማሰባሰብ ቢቻልም በመሰረተ ልማት እጦት ምክንያት የተበተኑት ዜጎች በርካታ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በታዳጊ ክልሎች ላይ ያለው የመሰረተ ልማት አቅርቦት በአሁኑ ወቅት በዚህ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የተገኘው "መሬት ላይ በማይታይ፤ ነገር ግን አመራሩ በሚያቀርበው የተጋነነ ሪፖርት ምክንያት ነው" ብለዋል። በቀጣይም በሁሉም ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር በሱማሌና በአፋር ክልሎች የተጀመሩ ስራዎች በሌሎችም እንዲሰፉ መደረግ አለበት ብለዋል።